ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን በመውሰድ ውጤታማ መሆን አለባቸው

95

ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) የፈጠራ ወሬዎችን ባለመስማት ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን በመውሰድ ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ እቴጌ መነን የልጅአገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ፈተናውን አስጀምረዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ በፈተና መስጫ ክፍሎች በመዘዋወር ተፈታኝ ተማሪዎችን አበረታተዋል።

የፈተናውን ሂደት አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በከተማዋ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ገልጸው ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።

ለፈተናው ሰላማዊ ሂደት የጸጥታ አካላት ከትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ልዩ ጥበቃና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የፈጠራ ወሬዎችን ባለመስማት ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን በመውሰድ ውጤታማ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የእቴጌ መነን የልጅ አገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ሃና ጸጋዬ፤ በትምህርት ቤቱ 74 ሴት ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የፈተና ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ግብዓት የሟሟላት፣ የጽዳት እንዲሁም የስነ ልቦና ዝግጅት ቀደም ብሎ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ባለሙያና በትምህርት ቤቱ የፈተና ጣቢያ ኃላፊ ወይዘሮ ገንዘብ ስንታየሁ፤ የዘንድሮው የፈተና ሂደት በልዩ ጥንቃቄ እንዲካሄድ ለማስቻል የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የታወጀበት በመሆኑ ከፈተናው በፊትም ሆነ በፈተናው ወቅት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ለተማሪዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም