አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር ለመጪዉ ትውልድ የማቆየት አደራ አለብን-የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት

አርባ ምንጭ ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ/)፡ አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር ለመጪዉ ትውልድ የማቆየት አደራ አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ፡፡
መንግስት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል የሀገር ህልውናን  ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከቀድሞው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የ50 አለቃ መስፍን መሳ  ለኢዜአ እንደገለጹት ንጹሃን ዜጎችን እንደ እንስሳ እያረደ ያለውን አሸባሪው ህወሓት ከአልሸባብ አሳንሼ አላየውም ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

''እኔ እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም'' ያሉት አስተያየት ሰጪው አሸባሪው ህወሓትን  በቆፈረው ጉድጓድ እንቀብረዋለን ብለዋል።

ህወሓት ግንባር ላይ ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ህዝቡን ተቀላቅሎ ሴራ እያሴረ መሆኑን ጠቁመው፤

''ህብረተሰቡ ይሄን  በማጋለጥ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይጠበቅበታል''  ብለዋል፡፡

የምዕራባዊያን መንግስታትና መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማ ያደረገ እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

''አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር  ለመጪው ትውልድ የማቆየት አደራ አለብን'' ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆኑት 50 አለቃ አብርሃም ያላ ናቸው፡፡

አፍጋኒስታን፣ ሊቢያና ሶሪያን ያፈራረሱ ምዕራባዊያን ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አሸባሪውን ህወሓት እንደመሣሪያ እየተጠቀሙ መሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክና ምስጥር ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት መቐለ ቀርቶ ቴንቤን በረሃ ቢገባም በገባበት ገብተን እንቀብራለን ያሉት አስተያየት ሰጪው "እኔ እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም" ነው ያሉት፡፡

በጋሞ ዞን ካምባ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ 10 አለቃ ታጌል ሽፈራው በበኩላቸው ከመከላከያ ሠራዊቱ፣ ከልዩ ሀይሉና ከሚሊሻው ጋር በመሆን አሸባሪውን ህወሓት  በመቅበር ሰላማችንን እንመልሳለን ብለዋል፡፡

''መንግስት ላስተላለፈው የክተት ጥሪ ባለቤቱ እኔ ነኝ'' ያሉት 10 አለቃ ታጌል፣ አሸባሪው ህወሓትና የውጭ አካላትን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ለ27 ዓመታት ሀገርና ህዝብን የዘረፈውን እብሪተኛ ሃይል ለመደምሰስ ሆ ብሎ ለተነሳው ህዝብ ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ የጋሞ ጎፋ ጥንታዊ የጀግና አርበኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ገሜዳ ናቸው፡፡

አባቶታችን በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር ከጠላት በመታደግ ወጣቱ የራሱን ታሪክ መፃፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የመከላከያ ሠራዊቱን የሚደግፍና አሸባሪዎችን ያወገዘ ሰልፍ በትናንትናው ዕለት መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም