ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ላይ በትኩረት እየሰራሁ ነው -አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ቶሌራ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እውቀትን ወደ ተግባር በመቀየር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቴክኖሎጅዎችን እያመረተ ነው።

ለግብርና፣ ለንግድና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች በመምህራንና ተመራቂ ተማሪዎች  መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በድምፅ ምግብ የሚያጎርስ ሮቦት፣ የጸሀይ ብርሀንን ለሀይል ምንጭነት ተጠቅሞ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ፣ የተፈላጊ ወንጀለኛ ማሰሻ መሳሪያ፣ የሙዚቃ ማቀነባበሪያ፣ ማየት ለተሳናቸው ሰዎች በስሜት ህዋሳት መልዕክት የሚያስተላልፍ አጋዥ ቴክኖሎጂዎች በዩኒቨርስቲው መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የብረታ ብረትና እንጨት ቅርጽ ማውጫ ማሽን፣ የሸንኮራ አገዳ ጁስ መጭመቂያና የወተት መናጫ፣ የለውዝ፣ የበቆሎና የጫጩት መፈልፈያ ማሽኖች መሠራታቸውን አመልክተዋል።

ከእነዚህ መካከል የኤሌክትሪክ ሃይል መቆጣጠሪያ፣ የሸንኮራ አገዳ ጁስ መጭመቂያ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ቅርጽ ማውጫ፣ የበቆሎ፣ የለውዝና የጫጩት መፈልፈያ ማሽኖችን ለአርሶ አደሮችና ለኢንዱስትሪዎች ለማሸጋገር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአዕምሮ ንብረት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍራኦል በቃና በበኩላቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ተኪ የሌላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

አርሶ አደሮች ለውዝና በቆሎ የሚፈለፍሉት እንዲሁም ወተት የሚንጡት በእጃቸው በመሆኑ ከፍተኛ የጊዜና የጉልበት ብክነት መኖሩን ጠቅሰው ማሽኖቹ ችግሩን እንደሚቀርፉ አስረድተዋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ የተመረቀው  አማኑኤል ቲቶ፤ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የወንጀል ተግባር ፈጽሞ የሚደበቅን ግለሰብ በሚሰጠው መረጃ መሰረት አነፍንፎ የሚጠቁም መሳሪያ መስራታቸውን ጠቁሟል።

"ቴክኖሎጂው አድጎ  ለአገልግሎት የሚበቃ ከሆነ የሀገር ሰላም ለማስጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው" ብሏል።

የህብረተሰቡን ኑሮ በችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ማዘመን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚጠበቅ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት  ዳይሬክተር  ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም