በአማራ ና ጋምቤላ ክልሎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና እየተሰጠ ነው

116

ጋምቤላ :ባህር ዳር ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል 127 ሺህ 272 ተማሪዎች የ12ኛ መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና መውሰድ መጀመራቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በጋምቤላ ክልልም በ21 የፈተና ጣቢያዎች ለ5 ሺህ 976 ተማሪዎች ፈተናው እየተሰጠ ነው።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ለኢዜአ እንደገለፁት ተማሪዎቹ ብሄራዊ ፈተናውን ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም ወስደው ያጠናቅቃሉ።

ፈተናው በ236 የፈተና ጣቢያዎች መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው ለተፈና ከተቀመጡ ተማሪዎች መካከል 119 ሺህ 447ቱ መደበኛ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የግል ተፈታኞች ናቸው።

በፈተና ጣቢያዎች የፀጥታ ኃይሎች ተመድበው ፈተናው በሰላም እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሸባሪው ህወሃት ወረራ በተፈፀመባቸው ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ዋግ ህምራና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ሙሉ በሙሉ፣ ሰሜን ሸዋና ሰሜን ጎንደር 5 ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፈተናው እንደማይሰጥም አስረድተዋል።

በነዚህ አካባቢዎች ለፈተና ይቀመጡ የነበሩ 36 ሺህ 835 መደበኛና የግል ተፈታኝ ተማሪዎች በወረራው ምክንያት ፈተናውን እንደማይወስዱ ተናግረዋል።

ተፈታኞቹ በቀጣይ አካባቢዎቹ ከወራሪው ኃይል ነፃ በሚሆኑበት ጊዜ ለተማሪዎቹ ፈተናው እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናውን በመስጠት 4 ሺህ 721 ፈታኝ መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች፣ የጣቢያ ኃላፊዎች እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል።

በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል ዛሬ በተጀመረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና በ21 የፈተና ጣቢያዎች ለ5 ሺህ 976 የመደበኛና የግል ተፈታኞች ፈተናው እየተሰጠ ነው።

በክልሉ የየብስት ትራንስፖርት በማይደርስበት የአኮቦ ጠረፋማ ወረዳ አስፈላጊው የፈተና ቁሳቁስ ከሁለት ቀናት በፊት በሄሊኮፕር እንዲደርስ መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም