ሕዝብ ተናገረ!

77

ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ከ30 ሚልዮን በላይ ሕዝብ ዐደባባይ ወጥቶ ስለሀገሩ ተናግሯል። ኢትዮጵያን ለማዳን እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት እንደሚከፍል፣ ለጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ፣ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል፣ የሕወሐትንና አጋር ጽንፈኛ ኃይሎችን ሀገር የማፍረስ የሽብር ተግባራት አጥብቆ እንደሚያወግዝ በግልጽ ተናግሯል።

እንዲሁም አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ የሚያስተላልፉትን የተዛባ መረጃ ሕዝቡ ኮንኗል። የሚያስተዳድረውን መንግሥት ነጻ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጡንና ይህንን ውሳኔውንም ዓለም እንዲያከብርለት ሕዝቡ አጥብቆ ጠይቋል።

ሕዝቡ ሀገሩን ለማዳን ማንኛውንም መሥዋዕትነት እንደሚከፍል በተግባር አሳይቷል። ሕዝቡ በወራሪው በተያዙ አካባቢዎችም በከፍተኛ ግለት እየተነሣ ነው። በተወረሩ አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ ጽንፈኛውን ሕወሐት ምቾት ተሰምቶት እንዳይቀመጥ እያደረገው ይገኛል።

ይህ የሕዝብ ንቅናቄ አሸባሪውን በሁሉም ቦታዎች እግር በእግር እየተከታተለ ርምጃ በመውሰድ አከባቢዎችን ተገድዶ እንዲለቅ እያደረገው ይገኛል።አሁን የተጀመረውን ለኢትዮጽያ ህልውና ሕዝብን የማዝመት ንቅናቄ በብዛትና በስፋት በማከናወን፣ አሸባሪውን ሕወሐትን ድል ማድረግ እንዳለበት ሕዝቡ በአንድ ቋንቋ ተናግሯል። ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚዘምትም አረጋግጧል። ወሳኙ ጉዳይ የውስጥ ዐቅማችንን መጠቀም መሆኑን ሕዝቡ በዐደባባይ አሳይቷል።

ሕዝብ ተናግሯልና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያዳምጥ ይገባል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም