ባለሀብቶች ለህልውና ዘመቻው ቃል የገቡት 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እየተሰበሰበ ነው- መምሪያው

77

ጎንደር ጥቅምት 28/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሀብቶች የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብለው የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ ቃል የገቡትን 20 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ስራ መጀመሩ ተገለጸ።
በጎንደር ከተማ ‘’ገንዘባችንና ህይወታችን ለህልውናችን’’ በሚል መሪ ቃል የከተማው ባለሀብቶች የክተት ጥሪውን በገንዘብና በቁሳቁስ መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የከተማው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት የከተማው ባለሀብቶች ሀገር ከሌለ ኢንቨስትመንትም ሆነ ሀብትና ንብረት ሊኖር አይችልም በማለት ለዘመቻው ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ ነው።

"ባሀለብቶቹ በህልውና ዘመቻው ወቅት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ከመለገሳቸውም በላይ በቁሳቁስና ሞራል በመስጠት ጭምር ሲደግፉ ቆይተዋል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የክተት ጥሪውን በመቀበል ቃል የገቡትን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የማሰባሰበ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በከተማው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ከ450 በላይ ባለሀብቶች እንደሚገኙ ጠቁመው ሀገራዊ የክተት ጥሪን በመቀበል ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በግንባር የዘመቱ ባለሀብቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

''አሸባሪው ህወሀት የአማራ ክልል በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲዳከም አልሞ እየሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡

"ባለሀብቱ ሰርቶና ነግዶ ሀብት የሚያፈራውና የሚጠቀመው ሀገር ሲኖር በመሆኑ የሽብር ቡድኑ የከፈተብንን ጦርነት በአጠረ ጊዜ ለመቋጨት የባለሀብቱ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

''ሰላም ከሌለ የእኛ ሀብትና ፎቅ ምንም አያደርግልንም፤ ስለሆነም በግንባር ለሚፋለመው የፀጥታ ሃይላችን ደጀን በመሆን የገንዘብም ሆነ የስንቅ ድጋፍ እያደረግን ነው'' ያሉት ደግሞ በኮንስትራክስን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብት አቶ መብራቱ ማሞ ናቸው፡፡  

በከተማው በኢንዱስትሪ መስክ የተሰማሩ ባለሀብት አቶ ሲሳይ አለማየሁ በበኩላቸው "ሀገር ሰላም ካልሆነ ብትሰራም ሆነ ብታተርፍ ደስተኛ ልትሆን አትችልም" ብለዋል።

"የሀገሬን ሰላምና የህዝቤን ደህንነት በማስቀደም ሁለት መኪኖዎቼን ለግዳጅ ሰጥቻለሁ" ያሉት አቶ ሲሳይ  "ለህልወና ዘመቻው ከ200ሺህ ብር በላይ  ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታዬን በመወጣት ላይ እገኛለሁ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በከተማው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብት  ወይዘሮ የሺ ደሴ በበኩላቸው "ሀብት ሁለተኛ ጉዳይ ነው፤ ዛሬ ላይ ህልውናችን ሊያጠፋ፣ መጠጊያና መጠለያችን የሆነችውን ሀገራችንን ሊያፈርስና ሊበትን የመጣን ጠላት መፋለም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡

"ባለሀብቱ ሀብቱን ለዘመቻው በመደገፍና የዘማች ቤተሰብን በመንከባከብ እንደ ሀገር የተደቀነብን ስጋት ለመቀልበስ ጦርነቱ በአጠረ ጊዜ እንዲቋጭ በጋራና በህብረት ጠንክረን መደገፍ ይኖርብናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በከተማው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሀብቶችን ጨምሮ የከተማው አመራሮች ተሳትፈዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም