ምዕራባዊያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ

74

ሐረር ፤ ጥቅምት 26/ 2014(ኢዜአ) አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን በማቆም እጃቸውን እንዲያነሱ በምሥራቅ ሐረረጌ ዞን የባቢሌ ከተማና አካባቢ ነዋሪዎች አመለከቱ።

ከ10ሺህ በላይ የሚገመቱ የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ በባቢሌ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ የውጭ ጣልቃ ገብነትን አጥብቀው እንደሚቃወሙ በጋራ ባሰሙት ድምጽ አስታውቀዋል

የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባሻገር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ሆነው መስዋዕትነት በመክፈልም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ  ተነሳስተዋል።

እንዲሁም በተደራጀ መንገድ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች ለጸጥታ ኃይሎች ስንቅ ማዘጋጀታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች ውስጥ አቶ ስንታየው በለጠ በሰጡት አስተያየት፤  አሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደልና ጭፍጨፋ ለማስቆም ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅቺያለሁ ብለዋል።

በተለይ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የወስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እያሳደሩ ያሉትን ጫና ተገቢነት ስለሌለው እጃቸውን እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔን በመደምሰስ በሀገሪቱ ሰላምና ልማት ለማምጣት የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ገልጸዋል አቶ ስንታየሁ።

''እኛ አንድ ነን ከፋፋይ የሆነው ህወሃት በፍጹም ኢትዮጵያን ዳግም አያገኛትም አሜሪካና ምዕራባዊያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ'' ብለዋል።

ወይዘሮ ወይንሸት ተካልኝ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል አሸባሪው ህወሃትን ግንባር ድረስ ሄደው ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ወጣቱና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ለትግሉ እንዲዘጋጅም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሸባሪዎቹ  ህውሃትና ሸኔን በመደምሰስ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን እየታኬደ ባለው ዘመቻ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት እንደሚፈልግ የተናገረው ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት ሙዘሚል ጀማል ነው።

የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትን ጫናን አጥብቆ እንደሚቃወም የገለጸው ወጣቱ፤ የውስጥ ጠላቶች  ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ የሚሸርቡትን ሴራ ለማክሸፍ የበኩሉን እንደሚወጣ ነው ያስታወቀው።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ ለሰልፈኞቹ እንደተናገሩት፤ የዞኑ ነዋሪዎች የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በአንድነት መቆሙን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ጀግናው መከላከያ ሠራዊትንም እንዲቀላቀሉና  በደጀንነት  የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፎች ዛሬ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መካሄዳቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተከታታይ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም