ዓዋጁ የሀገር ደህንነትና ሰላምን ያስጠብቃል- የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

54

ሚዛን አማን ጥቅምት 26/2014( ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ የህዝብና የሀገር ደህንነትና ሰላምን የሚያስጠብቅ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁራን አስታወቁ።

 በዓዋጁ ትግበራ የመብት ጥሰቶች እንዳያጋጥሙ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ዓዋጁ ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና አደጋ በመመከት ደህንነቷንና ሰላሟን ለማስጠበቅ ያስችላል።

"ዓዋጁ የአገር ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 93 መሠረት አድርጎ መታወጁ ተገቢና ወቅታዊ ያደርገዋል" ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር ታደሠ አይበራ ዓዋጁ ሽብርተኛው ህወሀት ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በሕዝብ ውስጥ የተሰገሰጉ ባንዳዎችን ለማጥራት ያስችላል" ብለዋል ።

አገር የማዳን ዘመቻውን በስኬት ለማጠናቀቅ ዓዋጁ መውጣቱ ተገቢና ትክክለኛ እንደሚያደርገው  አስታውቀዋል።

የሽብር ተግባር በባህሪው በአንድ ቦታ የሚገደብ ባለመሆኑ አሸባሪው በየቦታው የጥፋት ወጥመዱን እንዳይዘረጋና የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመገደብ ረገድ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን መምህር ታደሠ አብራርተዋል።

በዓዋጁ አፈጻጸም የዜጎች መብት ጥሰት እንዳይፈጸም በአስፈጻሚ አካላት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

"በየአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ስር ነቀል የመፍትሔ እርምጃዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው" ብለዋል።

ዓዋጁ በሕዝብ ዘንድ በአግባቡ እንዲታወቅ ማድረግና በአተገባበሩ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ መሰራት እንደሚገባው ምሁሩ አሳስበዋል።

ሌላው የዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር አዳነ ኮርቦ እንደተናገሩት ዓዋጁ ባንዳዎችን ከሕዝቡ መካከል ለማጥራትና ሕግ የማስከበር ሥራን ለማጠናከር ያስችላል።

ዓዋጁ ለመደበኛ የፀጥታ አካላት አቅም በመፍጠር አገር ላይ የተጋረጠን ፈተና ለመሻገር ድልድይ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ህልውና በመፈታተን ላይ የሚገኘውን ሽብርተኛውን ህወሃትና ጀሌዎቹን ለመደምሰስ እንደሚረዳ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ዓዋጁ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዳለው የተናገሩት መምህር አዳነ በፍጥነት ወደ ትግበራ መገባት እንዳለበት ያሳስበዋል።

በዓዋጁ ትግበራ የመብት ጥሰቶች እንዳያጋጥሙ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች መጣስ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል።

"በተለይ በአንቀፅ 25 ላይ የተቀመጠውን የእኩልነት መብት በመጠበቅ ዘር፣ ጎሣና ሃይማኖት ሳይለይ ተፈጻሚ መሆን ይገባዋል" ብለዋል።

በሚኒስተሮች ምክር ቤት የሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደነቀውን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም