"ኢትዮጵያን አፍርሼ እረማመድባታለሁ" ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በጋራ ክንዳችን እናፈርሰዋለን

73

ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያን አፍርሼ እረማመድባታለሁ" ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በጋራ ክንዳችን እናፈርሰዋለን ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

ኢትዮጵያዊያን ለ27 አመታት ግፍና በደሉን ተሸክመው ቆይተው መከራው ሲበረታባቸው "በቃህ" ብለው ያሽቀነጠሩት አሸባሪው ህወሃት "ኢትዮጵያን ሳላፈርስ ወደ ሲኦል አልገባም" በማለት የቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን በበላይነትና በፍፁም አምባገነናዊነት በመራባቸው ዓመታት በዜጎች ላይ አስቦ ያልፈፀመው ክፋትና በደል አልነበረም።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን የህዝብ ብሶት አሸቀንጥሮት መቀሌ ከከተመ በኋላም "እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት" በማለት አገርና ድንበር ጠባቂ ሰራዊት በማጥቃት ክህደቱን አሳይቷል።

አሸባሪው በፈፀመው ወንጀል መንግስት ተገዶ ወደ ህግ ማስከበር በገባበት ወቅት ወደ በርሃ ተበታትኖ የነበረው ሃይል ቆይቶ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረጉ እንደገና ተሰባስቧል።

ቡድኑ ከተሰባሰበ በኋላም ከህፃናት አስከ አዛውንት ለጦርነት አሰልፎ በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈፀም ንጹሃንን በመግደል፣ የቤት እንስሳትን ጨምሮ ንብረት በመዝረፍና በማውደም የጭካኔ ተግባሩን አሳይቷል።

በመሆኑም "ኢትዮጵያን አፍርሸ እረማመድባታለሁ" ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በጋራ ክንዳችን እናፈርሰዋለን ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ከንቱ አላማ መቼም ቢሆን የማይሳካ ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ የኢትዮጵያ ልጆች ከንቱ ህልሙን አምክነው መዳረሻውን "ሲኦል" ያደርጉታል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ ሁሉም ማእዘናት በመንቀሳቀስ ''በደምና በአጥንቴ መስዋዕትነት ከፍዬ የማድናት እኔ ነኝ'' በማለት አሸባሪውን እየተፋለሙት መሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።

በጠላት ላይ በጋራ መነሳትና መዝመት የኢትዮጵያዊያን መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ሁሉም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ "ሲኦል እገባለሁ" በማለት ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም