ወጣቶች ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀላቀል የዜግነት ግዴታቸው እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

57

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀላቀል ሀገርን ለማዳን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ አሸባሪው ህወሃትንና የውጭ  ጣልቃ ገብነትን  የሚቃወም  ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የሻሸመኔ ከተማ  አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ኦሾ ከድር እንደገለጹት፤  በሴራና  በተንኮል ፖለቲካ የተሸበበው  አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ዘመኑ በሀገሪቱን ህዝቦች ላይ የፈጸመው በደልና ግፍ ተቆጥሮ አያልቅም።

ይህን እኩይ ተግባሩ የመረራቸው መላው ኢትዮጵያዊያን ታገለው ከጫንቃቸው ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገዱን አስታውስዋል።

ሆኖም በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ የተመረጠው መንግሥት ፊቱን ወደ ልማትና ብልጽግና ባዞረበት ማግስት አሸባሪው ሕወሓት ወረራውን በማስፋፋት  በሀገር ላይ  ክህደት  ፈጽሟል ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን እየተፈጸመ ያለውን ወረራና ዘረፋ በመመከት    የሀገር ህልውና የማስጠበቅ ተግባር ላይ መረባራብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

መላው የሻሸመኔ ነዋሪ ህዝብ እና አመራሩ ሀገርን ለማዳን  የሚደረገውን  ትግል ከሁሉም ተግባር ቅድሚያ ሰጥተው መደገፍ እንዳለበት  አመልክተዋል።

በተለይ የከተማዋ ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ከጀግናው  የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀላቀል ሀገርን ለማዳን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የህልውና ዘመቻው በአጠረ ጊዜ እንዲቋጭ መላው የከተማዋ ነዋሪ ከዚህ በፊት ልጆቹን መርቆ በመላክ ያደረገው  ተሳትፎ አጠናክሮ በመቀጠል ሀገራችን ለየትኛውም  የዓለም ተጽዕኖ እንደማትንበረከክ ሊያሳይ ይገባል ብለዋል ከንቲባው።

ከሰልፉ ተካፋዮች መካከል አቶ አብደላ ዋቆ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው ቡድን በስልጣን ዘመኑ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው  በደል  ሁላችንንም  ሲንገበገብ ቆይቷል ብሏል።

ይህ ሳያንሰው ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣውን ለውጥና የብልፅግናውን ጉዞ  ለማደናቀፍ   ሴራ ሸርቦ  ዳግም መምጣቱን  በመቃወም  በሰልፉ ላይ  መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ቡድኑ አሁን ላይም  በሀገሪቱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸው፤ ሁሉም ነገር ከሀገር ስለማይበልጥ የግዳጁ አካል ለመሆን መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

ወጣት መስከረም ላራጎ በበኩሉ፤አሸባሪው ህወሓት የህዝብ ለህዝብ ግጭት  እንዲፈጠር  ምክንያት ከመሆን ባለፈ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ክህደት የፈፀመ ባንዳ ብሏል።

የሀገር ጠላት የሆነውን ይህንን ቡድን  ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ሊታገለው መዘጋጀቱን ገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊታችንና የፀጥታ ኃይላችንን ለመደገፍ የምንሳሳለት ሀብትና ጉልበት የለንም ያለው ወጣቱ፤ የህወሓት ግበዓተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ እረፍት እንደማይኖረው አስታውቋል።

በህዝባዊ ሰልፉ ላይ ከሻሸመኔ ከተማ  ቀበሌዎች የተውጣጡ   ወጣቶች፣  ሴቶች ፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ከፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም