አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠሩት ያሉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ ተጠየቀ

70

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት26/2014(ኢዜአ) አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት መንግስታት በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።
ነዋሪዎቹ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገርን ከአሸባሪው  ህወሃት እና ተላላኪዎቹ የጥፋት ሴራ ለማዳን እንደሚረባረቡም አስታውቀዋል።

የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር እየተካሄደ  ባለው ዘመቻ  ግንባር ድረስ  በመዝመት ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።

የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን  ከአገዋ ተጠቃሚነት ማገዱ  ደሃውን ሀብረተሰብ የሚጎዳ በመሆኑ  ተፈጻሚ እንዳይሆን ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን በጋራ አሰምተዋል።

አንዳንድ የምዕራባውያን መንግስታት በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ እየፈጠሩት የሚገኙትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙና  ሀገራችን ህልውናዋን ለማረጋገጥ የያዘችውን እውነት በአግባቡ መረዳት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል ታዋቂው የድሬዳዋ አፋን ኦሮሞ ገጣሚ ሻሜ መሐመድ ፤ሀገር የማዳን ጉዳይ በእያንዳንዳችን ትከሻ ላይ ያረፈ ወቅታዊ ኃላፊነት በመሆኑ በዕውቀቴ የጠራ መረጃ ለህዝብ ከማቀበል ባለፈ  ባለኝ ገንዘብና ጉልበት ለማገዝ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

ወጣት ጃማ ሐሰን በበኩሉ፤ ሀገር የሌለው ሰው እንደ ሶሪያና የመን መሆኑ ስለማይቀር  ሀገሬን ከህውሃት አሸባሪ ቡድን ለማዳን ዝግጁ መሆኔን ለማረጋገጥ በሰልፉ ላይ ተሳትፌያለሁ ነው ያለው።

እያመረቱ ሀገርን ከወያኔ ለማዳን ያላቸውን ሃብትና ንብረት ለሠራዊቱ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ  በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ አርሶ አደር  አህመድ ኑር ናቸው።

ወይዘሮ ፍሬህይወት አለሙ፤ ሀገርን ከአሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎች ለማዳን  ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለመዋጋት ቆርጠናል ብለዋል።

ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን በየቀበሌው ተደራጅተው ስንቅ የማዘጋጀቱ ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም እንዲሁ።

የምጣኔ ሃብት ሙያ ተማሪ አብዱረህማን አህመድ በበኩላቸው፤ የአሜሪካ መንግስት አገዋ በሚል መሪ መርህ ደሃ  ሀገራት ከቀረጥ ነፃ የጨርቃ ጨርቅ ና አልባሳት ምርቶችን ወደ ሀገሯ መፍቀዷ ሀገራቱንና ደሃ ህዝባቸውን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

ሆኖም  ይህን ነፃ እድል ባልተረጋገጠ ዴሞክራሲ መብት ተጥሷል በሚል ጊዜያዊ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ መጣሏ  በርካታ  ዜጎች የሚጎዳ በመሆኑ  ማንሳት እንዳለባት አመልክተዋል።

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ መኮንን ታደሰ፤ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት መንግስታት እና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መታቀብ አለባቸው፤ እኛም  ሆንን  በመላው አለም የሚገኙ ዜጎች ድምፃቸውን ማሰማት ይኖርብናል ብለዋል።

ከጀግና የመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገርን ለማዳን ግንባር መሰለፍ ታላቅ ክብር በመሆኑ ለመዝመት ተዘጋጅቻለሁ ያለው ደግሞ ወጣት ስንታየሁ ተስፋዬ ነው።

የአሸባሪው ተላላኪዎች በማጋለጥ  ለህግ አሰልፈን በመስጠት የአካባቢውን ሰላም እየጠበቅን እንገኛለን ብሏል ወጣት ስንታየሁ።

ዛሬ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች    ለሠራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ በገለጹበት ሰላማዊ ሰልፍ ሥነ-ሥርዓት ላይ  ተመላሽ የነበሩ የሠራዊት አባላት ዳግም ወደ ግንባር በክብር ተሸኝተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ፤ህዝባችን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደረገ የሚገኘው ሁለንተናዊ ዕገዛ በታሪክ ማህደር ደምቆ የሚፃፍ ይሆናል ብለዋል።

ከሃዲው  አሸባሪ ህወሓትና ተላላኪዎቹን ከመገርሰስ ባሻገር የተፈናቀሉ ወገኖቻችን እየተደረገ ያለው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተለይ ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ህዝብን በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል ከአወደ ውጊያ ባሻገር ያለውን ጀግንነት ማሳየት እንዳለበት ከንቲባ ከድር አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም