ብሔራዊ የጂኦስፓሻል መረጃ ማዕቀፍ በዓመቱ አጋማሽ ተግባራዊ ይደረጋል

93

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) ብሔራዊ የጂኦስፓሻል መረጃ ማዕቀፍ በተያዘው ዓመት አጋማሽ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚተገበር የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ የተቀናጀ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ማዕቀፍ የድርጊት መርሃ-ግብርን አስመልክቶ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ተቋማት ሙያተኞች ጋር እየመከረ ነው።

'የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ማዕቀፍ' በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ግቦችን እንዲሁም የአገራትን የእድገት አጀንዳዎች ለመተግበር የሚካሄድ የመረጃ ማሰባሰቢያ ሂደት ነው።

የጂኦስፓሻል መረጃ ምን የት ቦታ፣ መቼ፣ በምን መጠን፣ ለምን እና እንዴት ተፈጠረ የሚሉ ወሳኝ መረጃዎችን ለውሳኔ ሰጪ፣ ለፖሊሲ አውጪና ለተጠቃሚ አካላት መስጠት የሚያስችል ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩትም የመሬት ምዝገባና አጠቃቀም ዕቅድ፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ፣ የከተማ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች አገልግሎቶችን በመተንተን መረጃዎችና ውጤቶችን የማቅረብ ሥራ ይከውናል።

የጂኦስፓሻል መረጃ ማዕቀፉን በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር እንዲቻል ኢንስቲትዩቱ ረቂቅ የድርጊት መርሃ-ግብር ያዘጋጀ ሲሆን ውይይቱ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ ነው።   

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ እንደገለጹት፤ የጂኦስፓሻል መረጃ ለፈጣን አገራዊ እድገት ወሳኝ ሚና አለው።

የድርጊት መርሃ-ግብሩን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት የፈጀ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው ዓመት አጋማሽ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የአገሪቷ የመረጃ ፍላጎትና ወቅታዊነት ላይ በመመስረት እየተሻሻለ የሚተገበር ይሆናልም ብለዋል።

ወቅታዊ፣ ከባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ብሎም ተፅዕኗቸውን ለመቀነስና ለመቆጣጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እየተተገበረ ባለው አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የጂኦስፓሻል መረጃን ከኮሙኒኬሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ማቀናጀት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በዚህ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘመን ተቋማት የጂኦስፓሻል መረጃን በቀላሉ የሚያገኙበት የፓሊሲ፣ የደረጃ እና የቴክኖሎጂ አሠራሮችን መዘርጋትም እንዲሁ።

ይህም በተቋሟት አማካኝነት ከሚሰጡ ውሳኔዎች ባሻገር ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ያግዛል።

በተጨማሪም የቀጣዩን 10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ከማሳካት አኳያ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በመሆኑም ጂኦስፓሻል መረጃን የሚተገብሩ ተቋማት ዳታ ከማምረት ባልተናነሰ የመረጃ ወቅታዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ውይይት አስተዳደራዊና ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ፣ ፋይናንስ፣ የዳታ አያያዝ፣ የደረጃ ምዘና፣ ቅንጅታዊ አሠራርና የአቅም ግንባታ በትኩረት የሚዳሰሱ አበይት ጉዳዮች ይሆናሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም