የመገናኛ ብዙሃን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል

125

ጥቅምት 25/2014 ( ኢዜአ )  የመገናኛ ብዙሃን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን  በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት ጥሪ አቀረበ፡፡
በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ያልተገቡ መልዕክቶች ታዳጊዎቸን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

የማህበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት ድግሞ በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል፡፡

የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት አስተባባሪ ወይዘሮ ዱረቲ ታደሰ እንደሚሉት፤ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በመሆኑም በመገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፉትን መልዕክት በጥንቃቄ መምረጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ማካተት ዳይሬክተር ወይዘሮ ወይንሸት ገለቶ በበኩላቸው

በሴቶች  ላይ  የሚደርሱ ጻታዊ ጥቃቶችን በውጤታማነት ለመከላከል ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ግልጽ የሆነ የውይይት ባህል ማዳበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃንና ኪነጥበብ ዘርፎች ኢትዮጵያ በስርዓተ ጾታ ዙሪያ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን አክብረው በመስራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት፡፡

በተለይ በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ሙዚቃዎችና ማስታወቂያዎች መልዕክትና ይዘት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን እንዳያባብሱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና በቤተሰብ ወስጥ ግልጸኝነት ለማስፈንም ''የሌሊት ጧፍ'' የተሰኘ ተከታታይ ድራማ በማዘጋጀት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱንም ነው የጠቆሙት፡፡

በድራማው ዝግጅት ላይ የተሳተፈችው አርቲስት መቅደስ ጸጋየ በበኩሏ ድራማው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በግልጽ እንዲያወሩ እድል መፍጠሩን ከተገኘው ግብረ መልስ መረዳት እንደተቻለ ተናግራለች።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን የሚጸየፍ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርባለች።

የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ትስስር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም