የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የልደት መታሰቢያ ስነ-ስርዓት በባህር ዳር ከተማ ተካሄደ

70
ባህርዳር ነሀሴ 13/2010 የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ማህበር የዳግማዊ አፄ ምኒልክ 174ኛ የልደት መታሰቢያ ስነስርዓት አካሄዱ፡፡ የመታሰቢያ ስነስርዓቱ የተካሄደው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት " ኑ ታሪካችንን እንወቅ፣ጀግኖቻችንን እንዘክር"  በሚል መሪ  ሀሳብ በተዘጋጀ ውይይት  ነው፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሙሉጌታ ይታያው በዚህ ወቅት እንደገለጹት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሀገራቸውን ዳር ድንበር  ከማስከበር ባሻገር ከነበሩበት ዘመን  ቀድመው የሚያስቡና የኢትዮጵያ ዘመናዊ መሀንዲስ ነበሩ። መላው ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ ከአድዋ ድል ጅምሮ ሀገሪቱን በልማትና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉ መሪ እንደነበሩም  አስታውሰዋል። ዶክተር ሙሉጌታ እንዳሉት አዲሱ ትውልድ ማንነትንና ሀገራዊ ሉአላዊነት ማስከበርን  ፣ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ የነጻነት አባት ለመባል የበቁትን ከእኚህ  አርቆ አሳቢ መሪ መማር ይገባል። "ዳር ድንበሯ ተከብሮ በቴክኖሎጂና በዘመናዊ አስተዳደር የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዘመናቸውን ሙሉ የደከሙ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መሰረት ናቸው " ያለው ደግሞ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ክንዱ ነው። ወጣቱ  ትውልድ የእርሳቸውን ሀገራዊ ፍቅር በመሰነቅ የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ምክንያታዊ ሆኖ ለሀገሩ እድገትና አንድነት ሊሰራ ይገባል። በመታሰቢያ ስነስርዓቱ ወላጆቻቸውን ላጡና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ችግረኛ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ  ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም