የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ13 የጤና ተቋማት የአምቡላን ቁልፍ አስረከበ

56
አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ለሰጡ 13 የጤና ተቋማት አምቡላንስ ሰጠ። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ ለመጣው ለውጥ ድጋፍ ለመስጠት በተጠራው ሰልፍ ላይ በፈነዳ ቦምብ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከመቶ በላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል። የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ባይሰጡ ኖሮ የሟቾችና የተጎጂዎች ቁጥር ይጨምር እንደነበር የጠቀሰው ከተማ አስተዳደሩ ''ተቋማቱ ላደረጉት ሙያዊና ሰብዓዊ እርዳታ እውቅና ይገባቸዋል'' ብሏል። በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ 13 ሆስፒታሎች ለእያንዳንዳቸው አንድ የአምቡላስ ቁልፍና የምስክር ወረቀት ከከተማ አስተዳደሩ ተበርክቶላቸዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ነው። ባለፈው ዓመት የ3 ሺህ 200 አምቡላንሶች ግዥ ተጠይቆ 1 ሺህ 500 አምቡላንሶች ግዥ የተከናወነ ሲሆን የ1 ሺህ 700ዎቹ በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በ2011 እና 2012 በጀት ዓመት ለ20 ሺህ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጭዎች ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ''በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉት የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ ተቋማትን የማጠናከርና ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እናከናውናለን'' ብለዋል። በመስቀል አደባባይ በተከሰተው አደጋ ያለባቸውን የግብዓት እጥረት በመቋቋም የሟችና ተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ያለውን የአምቡላንስ እጥረት ለመቀነስ ግዥ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው በጀት ዓመት ለአምቡላንስ መግዣ 49 ሚሊዮን ብር መድቦ 47 አምቡላንሶችን በመግዛት በከተማዋ ያሉትን አምቡላንሶች ቁጥር 69 ማድረሱን ገልጸዋል። ከዚም ባለፈ በቀጣይ አደጋዎች ሲከሰቱ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላ ይደረጋል፤ ለባለሙያዎችም ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም