የሀገር አፍራሽና የውጭ ተላላኪውን የሽብር ቡድን የስግብግብነት ሩጫ ለመግታት የክተት ጥሪውን ተቀብለናል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር አፍራሽና የውጭ ተላላኪውን የሽብር ቡድን የስግብግብነት ሩጫ ለመግታት የክተት ጥሪውን ተቀብለናል

ደብረ ብርሃን፣ ጥቅምት 22/2014 ( ኢዜአ ) ሀገር አፍራሽና የውጭ ተላላኪው የሽብር ቡድን አሁን ላይ የሚያደርገውን የስግብግብነት ሩጫ መንገድ ለመግታት የመንግስትን የክተት ጥሪ መቀበላቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በከተማው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ምክትል ሰብሳቢ መቶ አለቃ ወንድ ወሰን ግዛው 'በአባቶቻችን ደም የተገነባችና ህዝቦቿ ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው የኖርንባት ወደ ፊትም የሚኖሩባት ኢትዮጵያ በወራሪ ሃይል አትደፈርም' ብለዋል ።
ሀገር አፍራሽና የውጭ ተላላኪው የሽብር ቡድን አሁን ላይ የሚያደርገውን የስግብግብነት ሩጫ መንገድ ለመግታት የመንግስትን የክተት ጥሪ መቀበላቸውንም ተናግረዋል።
''ደማችን ሃገራችን ነች'' ያሉት መቶ አለቃ ወንድወሰን ''በሃገር ሉአላዊነት ላይ አንደራደርም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ሳንሰስት እንከፍላለን'' ብለዋል።
የማህበሩ አባላት ከመንግስት የክተት ጥሪ ቀደም ብለውም በሀገር መከላከያ ስር ጥያቄ አቅርበው ለዘመቻው ተዘጋጅተው መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ገሚሶችም ግንባር ዘምተው ቡድኑን እየተፋለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
አሁንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያን ጠላት በመንቀል ሰላሟን ለማረጋገጥና ወደ ነበረችበት ክብሯ ለመመለስ የክተት ጥሪውን ተቀብለው አባላቱ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
የአሸባሪውና የውጭ ቅጥረኛ የህወሃት ቡድን ሀገርን የመበተን ህልሙ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ለመደምሰስ የክተት ጥሪ መቀበላቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ ደምሰው ዘለቀ ናቸው።
በወንበዴው ወራሪ ሀይል ሀገር ስትተራመስና ስትፈርስ ከማየት በላይ አሳፋሪ ታሪክ እንደሌለ ጠቅሰው፤ “እጃችንን አጣጥፈን ተቀምጠን ሞትን አንጠብቅም የክተት ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል” ይላሉ።
“በሀገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችን እና አገራዊ እሴቶቻችን ላይ የሽብር ቡድኑ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽሟል” ያሉት ደግሞ በደብረ ኢጳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አየለ ግዛቸው ናቸው።
ይህ ቡድን የሃገርን እሴት ከማውደምም በላይ ሃገሪቱ ከማትወጣበት የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ከቷት ለማለፍ እያደረገ ያለውን የጨለማ ጉዞ በተባበረ ክንድ ለመግታት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
የመማር ማስተማር ሥራ የሚከናወነው ሀገር ሰላም ስትሆን መሆኑን በመገንዘብ ለዘመቻው መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን የሴራ ጉዞ ለመግታት የክተት ዘመቻ መታወጁ ይታወቃል።