በሰሜን ሸዋ የተከሰተው ቆርምድ የተባለ የባቄላ በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

163
ደብረ ብርሃን ነሀሴ 13/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን በ839 ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተውን ቆርምድ የተባለ የባቄላ በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑ የዞኑ የግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰበል ልማት ቡድን ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሽፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት በሽታው የተከሰተው በ10 ወረዳዎች  581 አርሶ አደሮች ባለሙት ማሳ ላይ ነው፡፡ ቆርምድ የተባለው የባቄላ በሽታ የሰብሉን  ቅጠል በማቆርፈድና በጣጥሶ በመርገፍ ፍሬ እናዳያፈራ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል። ለመከላከል በተደረገው ጥረትም 455 ኪሎ ግራም ኬሚካል በመርጨት 381 ሄክታሩን ከበሽታው ነጻ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ቀሪውንም በተመሳሳይ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በሽታው  በይበልጥ የሚከሰተው በርጥበታማና ውሃ በሚያቁር ቦታ ላይ በመሆኑ አርሶ አደሩ ማሳውን በማጠንፈፍና ፈጥኖ ኬሚካል በመርጨት ሊከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በአንድ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ ባቄላ መዝራትም ለበሽታው መከሰት ምክንያት በመሆኑ  አርሶ አደሮች እያፈራረቁ በሌላ ሰብል በማልማት  መከላከል እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡ የባቄላ ምርት የገበያ ፍላጎትና ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ አርሶ አደሩ ልማቱን የማስፋፋቱ ስራ መቀጠሉን ያመለከቱት ባለሙያው ከርሶ አደሩ  ጋር በመሆን በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ በባሶና ወራና ወረዳ የዲቢላ ቀበሌ  አርሶ አደር አባባየሁ ሽሁ አንድ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት ባቄላ በቆርምድ በሽታ በመጠቃቱ በባለሙያ እገዛ ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ጥረት  እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ “የበሽታውን መቀነስ  በማየቴም ለማግኘት ያቀድኩትን እንደማሳካ እምነቴ ነው”  ብለዋል፡፡ በወረዳው  የቃሲማ ቀበሌ  አርሶ አደር ላይከ አደናግር በበኩላቸው  በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት ባቄላ በቆርምድ በመጠቃቱ በኬሚካል ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ያቆረውን ውሃ በየቀኑ እንዲፋሰስ በማድረግና በማጠንፈፋቸው በሽታው  እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ በተያዘው የምርት ወቅት ከ40 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ከተዘራው  የባቄላ ሰብል ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም