የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚያደርሱት የአካባቢ ተፅዕኖን ለመቋቋም አዋጭነት ጥናት ግምገማ ሊኖራቸው ይገባል

141

ቢሾፍቱ ፤ ጥቅምት 20/2014(ኢዜአ)  የግንባታም ሆነ የሌሎች ማዕድን ልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሊኖራቸው የሚችለውን የአካባቢ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአዋጭነት ጥናት ግምገማ ሊኖራቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብዘሃ ህይወት ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የግንባታ ማዕድን ቁፋሮ በብዘሃ ህይወትና አካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

በተለይ ለስሚንቶ ግብዓትና ሌሎች ማዕድን ልማት ላይ የሚውሉ መሬቶች እጅጉን የተጉዱ ከመሆኑም ባለፈ ለብዘሃ ህይወት መመናመን መንስኤ እየሆኑ ናቸው ብለዋል።

"በቀጣይነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የኢኮ ቱሪዝም ማሳደግ በተለይ የሎጂና ቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ብዘሃ ህይወት ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ፣ በመሬት አጠቃቃምና አያያዝ ላይ በዋናነት መስራት አለብን" ነው ያሉት።

"85 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ብዘሃ ህይወት እየተጎዳ ያለው በሰው ሰራሽ በመሆኑ ለነገው ተተኪ ትውልድ የምትሆን ሀገር እንዲኖረን የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ማስቻል ቀዳሚ ስራችን መሆን አለበት" ብለዋል።

የግንባታም ሆነ የሌሎች ማዕድን ልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሊኖራቸው የሚችለውን የአካባቢ ተፅዕኖ ለመቋቋም አዋጭነት ጥናት ግምገማ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አሶሴሽን ፎር ዴቬሎፕመንት ኤንድ ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንዘርቬሽን ፕሮጀክት ሃላፊ አቶ ከተማ ፉፋ በበኩላቸው፤ በቢሾፍቱና አደአ ወረዳ 1ሺህ 70 ሄክታር በሰው ሰራሽ የተጎዱ መሬቶች ከመንግስት ተረክበው መልሶ ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በተለይ በቢሾፍቱ አካባቢ በሚገኙ የኪሎሌ፣ ቡልበላ ሃይቆችና በሲሚንቶ ማዕድን ቁፍሮ የተጎዳው የድሬ ተራሮች ላይ እየሰራን ነው" ብለዋል ።

ከተማዋና አካባቢው ያሉ ሃይቆችን ከብክለት መከላከልና የውሃ ይዘት እንዲለመልም መጠበቅ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ የጥናትና ምርምር ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህም  በሰው ሰራሽ ችግር የተራቆተው ቦታ መልሶ እንዲያገግም የስነ ምህዳር ጥበቃ ፣ የአፈር፣ የደቂቅ አካላት፣ እንስሳትና የብዘሃ ህይወት ጥበቃ ላይ እንዲሁ።

በተለይ የተፈጥሮ ሀብቱ እየተመናመነ ከመሆኑም ባለፈ የአየር ብክለት እያስከተለና የሀገሪቷ የስነ ህይወታዊ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል ።

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም አጠናክሮ ማስቀጠል፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተራቆቱ መሬቶች መልሶ እንዲያገግሙ የልማት ፕሮጀክቶችን መቅረፅ፣ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግና በኢኮ ቱሪዝም ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

ለእርሻ የሚሆኑና የአርሶ አደሩን መሬት ለኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ከማዋል ይልቅ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተጎዱ ምርት የማይሰጡ መሬቶችን መጠቀም ለትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል ይገባናል ነው ያሉት።

በአካባቢ ልማትና ጥበቃ ወጣቶች፣ ሴቶችና አጋር አካላትን በስፋት ማሳተፍ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም አመልክተዋል ።

በቢሾፍቱ ከተማ ፣አደአ ወረዳ፣ ኪሎሌና ቡልበላ ሃይቆች ላይ የኢኮ ቱሪዝምና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማልማት ስራ ውጤታማ በመሆኑ በቀጣይነት ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው።

ፕሮጀክቶቹ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት በተገኙበት  ተመርቀው  ኢኮ ቱሪዝምን ጨምሮ  ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም