የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል - ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ

51
አዲስ አበባ ነሓሴ 13/2010 የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካት በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የምረቃ ስነ-ስርዓት በዛሬው እለት እየተካሄደ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ እነዚህን መሰል ፕሮጀክቶችና የሃይል ማመንጫዎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ማርካት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የእያስመዘገበች እንደምትገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ስራውን ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ በሚቀጥሉት ሰባት አመታት “ብርሃን ለሁሉም ” የሚለውን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሲሆን ወጪው ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ነው። ከአምስት አመት በፊት በ2006 ዓ ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በአመት በአማካይ 185 ጊጋ ዋት ያመነጫል፡፡ ኃይል ለማመንጨት በቀን 1 ሺህ 400 ቶን ደረቅ ቆሻሻ በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም