ለሒሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶች ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታ ለማጎልበት እየተሰራ ነው

85

ዲላ፤ ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም (ኢዜአ) ለሒሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶች ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

"በኢትዮጵያ የሒሳብ እና የሳይንስ ትምህርቶች ተግዳሮትና ተስፋዎች" በሚል መሪ ሀሳብ ሚኒስቴሩ ከዲላ ዩኒቨርሲቲና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የመጀመሪያ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ አካሂዷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሒሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕከል ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም አለማየሁ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሀገሪቱ እድገት የማይተካ አስተዋጾ አለው።

"ይሁንና በዘርፉ አቅምና የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ደግፎ በማብቃትና በዘርፉ ሥራ ከመፍጠር አንጻር ውስንነት አለ" ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት የመምህራንን አቅም ከማጎልበት ጀምሮ የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ የሒሳብ እና የሳይንስ ትምህርቶች መሞከሪያ ማዕከላትን የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህም በታችኛው የእርከን ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶችን የግብዓት ችግር ከማቃለል በተጨማሪ ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲለማመዱ እድል ይሰጣል" ብለዋል።

በተጨማሪ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ማጠናከርና ማስፋት እንደሚያስችላቸው ነው ደክተር አብርሀም ያመለከቱት።  

የፈጠራ ሥራዎች የስራ ዕድል ከመክፈት ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖራቸው አስተዋጾ የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ዓለም አቀፍ የኢስትም ፓዎር የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ስሜነው ቀስቅስ ናቸው።

ይህም ሆኖ የፈጠራ ሥራዎችን አወዳድሮ እውቅና ከመስጠት ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጾ እንዲኖራቸውና ለገበያ ከማቅረብ አንጻር ውስንነት አለ ነው ያሉት።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምህንድስና ዘርፍ የተግባር ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ ተማሪዎች ፈጠራቸውን አበልጽገው ገቢ እንዲያመነጩ ማዕከል በማቋቋም ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ ክፍሌ በበኩላቸው፤ ኮንፍረንሱ  የተበታተኑ የምርምር ውጤቶችን ከማሰባሰብ በተጓዳኝ ለፖሊስና ለቀጣይ ስራ ግብዐት ለመውሰድ የተመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ስራ ያላቸውን ከ2ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ በማሰባሰብ ስልጠና ሰጥቷል።

በፈጠራ ሥራቸው የተሻሉትን ስምንት ተማሪዎች በመለየትም በፕሮጀክት አቅፎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ለተለያዩ ችግሮች ምላሽ መስጠት የምንችለው የፈጠራ ስራዎችን ስናበረታታ ነው" የሚሉት ዶክተር ደረጀ፣ በናሙና ደረጃ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የጥናትና ምርምር ኮንፈረንሱን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን የተሻለ ስራ ላቀረቡት እውቅና ተሰጥቷል።

በመድረኩ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላትና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም