በሴቶችና ህጻናት ላይ ግፍ የሚፈጽመውን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለመመከት የሚጠበቅብንን ድጋፍ እናደርጋለን

81

ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሴቶችና ህጻናት ላይ ግፍ እየፈጸመ የሚገኘውን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለመመከት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴት አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የአሸባሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ ከመጨፍጨፍ ባሻገር ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል፤ ህጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል፡፡

በተጨማሪ ሴቶችንና ህፃናትን በማፈናቀል የስነ-ልቦና ጫና ከመፍጠሩም በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ህይወታቸውን እንዲመሩ አድርጓል፡፡በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሴት አርሶ አደሮች አሸባሪ ቡድኑ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ግፍ ለመፈጸም ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ በተባበረ ክንድ ቡድኑን መመከት እንዳለበት ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደር ወይዘሮ አበባዬ ካሳው ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅና ጓንት ሆኖ አሸባሪውን ህወሓት ማስወገድ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

በየአካባቢው ያሉ ሴቶች ለሰራዊቱ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለዘመቻው ስኬት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦር ዞን የሚኖሩት አርሶ አደር ወይዘሮ አጀቡሽ ገዛኸኝ በበኩላቸው ''ሰላም ከሌለ ተንቀሳቅሶ መስራትና መኖር አይቻልም'' ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ሴቶች በተለይም ደግሞ እናቶች ልጆቻቸውን ስለሀገር አንድነትና ሰላም ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

"ወጣቱ አገርን ከጠላት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እናቶች ልናግዝ ይገባል" ያሉት በአማራ ክልል የባህርዳር ዙሪያ አካባቢ አርሶ አደር ወይዘሮ አቻሽ አላምር፤ ወጣቶች የመከላከያ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ከማበረታት ጀምሮ ለህልውና ዘመቻው ስኬት እናቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም