‹‹ዋ ! ያቺ “ቀን” የተረገመች ትሁን! ›› አሸባሪው ትህነግ

177

ጁንታውን እዚህ ዘግናኝ መቀመቅ ውስጥ የከተተው የፈፀመው ግፍ ፅዋ ሞልቶ በመፍሰሱ ነው። ለዚህ አሸባሪ ቡድን አሁን ያለበት አዘቅት ጥልቅና ድብን ያለ ጥቁር መቀመቅና ጨለማ ነው። ለወያኔው የሽብር ቡድን አሁን ያለበት ክስተት ከገነት ሲዖል የተወረወረ ያህል እልም ያለ ጨለማ ውስጥ የገባበት አስደማሚ አዘቅትም ነው።

ይህ ከንቱ የሽብር ቡድን ከዚህ ጥልቅና ስምጥ የሲዖል ሸለቆ ለመውጣት ሲቧጥጥ ቢውል፣ ሲያጠፋ ቢከርም፣ ሲጨፈጭፍ ቢኖር ቅንጣት አይሰማውም። ቀድሞ በነበረበት እንደ ገነት ኑሮ በሚያስበው የዘረፋና የጭቆና ዘመኑ ሆኖ፣ ይህን የሚመኘውን ግን ደግሞ ፈፅሞ መልሶ የማያገኘውን ቅዥት መልሶ ለመቆናጠጥ ይዋሻል፤ ያጭበረብራል፣ ያደናግራል፤ ይለፍፋል፤ መግለጫ ያወጣል፤ ድል ልቀዳጅ አፋፍ ላይ ነኝ ይላል። ይህ አስነዋሪና ጨፍጫፊ ቡድን፣ ሞቱን እንኳ ባለመረዳቱ፣ ዛሬም ትልቅና ህያው ነኝ ብሎ ለመስበክ ይዳዳል።

ቤታችሁን ዘግታችሁ ተቀመጡ ምንም አትሆኑም አትውጡ ይላል፤ በዚያች ትንሽ ልቡ ዛሬም ያፌዛል፣ ይቀልዳል፤ ይፎክራል።ይቺ ያበጠች ትንሽዬ ልብ ሰብዓዊነት በማይሰማው የቀጨጨ ማንነቱ ውስጥ ገብታ የምትጉላላ በጣዕር ላይ ያለች ነፍስ ያህል ሆና ትሰማለች። አላቅሙ መንጠራራቱ ያመጣው መዘዝና የጭካኔና ግፍ ሙላት ያስከተለው ኢትዮጵያዊ መልስ ምት ወያኔን ዶግ አመድ ጨምሮታል።አሸባሪው ወያኔ መርገም ያለበት ጥቅምት 24/2013 በግፍ የሰነዘራት ሰይጣናዊ እጁን ነው። ያቺ እጅ እንድትሰነዘር አብዝቶ ሲወተውትና እንዲፈፀም ሲታትር የነበረ ሰይጣናዊ አመራሩን ነው። ከመቀሌ ፓላስ ወደ ተንቤን ዋሻ የእውር ድንብሩን እንዲተምና የጉንዳን ጉዞ እንዲጓዝ ያደረገው እብሪቱንና ጥጋቡን ነው።

አሸባሪው ትህነግ << ዋ ! ያቺ ዕለት የተረገመች ትሁን! >> ማለት ነው ያለበት። እውነትም ያቺ እለት ለወያኔ የተረገመች ናት። ያቺ የእብሪት እለት አሸባሪው ወያኔን ሲዖል የጨመረች፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት ያጠናከረች፣ ያገማመደች፣ በቃሽ ወያኒት ያስባለች ድንቅ ግን አሰዛኝና የማትረሳ እለት ናት።ነፍሱን ብቻ ሳይሆን ካለችው ደመወዝ ላይ ሲያበላ፣ ሲያጠጣ፣ ሲያስተምር፣ መኖሪያ ሲገነባ፣ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላ ሲያቆም፣ አንበጣ ሲከላከል፣ ሰብል ሲሰበስብ፣ መንገድ ሲሰራ ወዘተ… የነበረውን የአገራችንን መከላከያ ሰራዊት ባላሰበበት፣ ባልገመተበት፣ ባልጠበቀበት ሁኔታ ወገንና ህዝብ አለኝ ባለበት አገሩ በግፍ የተቀላበት፣ የተጨፈጨፈበት የወያኔን መርዘኝነትና አሸባሪነት ዓለም በገሀድ ያወቀበት መጥፎ፣ ግን የማትረሳ እለት ናት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም።

ጥቅምት 24 ጁንታው ግፍ የፈፀመበት ብቻ ሳይሆን የመቃብሩን ጉድጓድ አጥልቆ የቆፈረበት የግብዓተ ፍፃሜው ድንቅ እለትም ናት። ያቺ ቀን መላው የሀገራችን ህዝብ ብሶቱን፣ አንድነቱንና አሸባሪውን ህወሓት ላይመለስ ሊቀብረው ቃል የገባባት፣ የወሰነባት እለትም ናት።ያቺ ዕለትና ቀን ትዕምርት ያላትም ናት። ከጥቅምት 24 በፊት የነበረው የወያኔ እብሪትና ድንፋታ ሙሉና በትዕቢት የተወጠረ ነበር፤ እግዜር የፈጠረውን ፈረስ በጁንታው አርማ ቀለም ቀብቶ አደባባይ በማዋል ይፈክር ነበር። ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው እያለ ሲያላዝንና ሲታበይ ነበር።

ጠንካራ ሀይል ገንብተናል፤ የሚሞክረን ያለም ብሎም ያቅራራ ነበር። ይህን እብሪትና ትዕቢት በ24 በተግባርና በጭካኔ ፈፀመው፣ መፈፀሙንም በኩራት አረጋገጠው። መብረቃዊ ጥቃት ብሎም አከበደው። ከሰማይ በታች የሚመክተው ሀይል እንደሌለም አገርም፣ ዓለምም ይወቀው ብሎ በድንፋታ አረጋገጠው። የጀግኖች ጀግና እሱ ጁንታው፣ በእሱ አጠራር ህወሓት መሆኑንም በኩራት ነገረው።ያቺን ቅፅበት እግዚዖ እንደሚልባት፣ ተምቤን ዋሻ የኋሊት እንደሚፈረጥጥባት፣ አማልዱኝ ብሎ ኤሎሄ እንደሚልባት፣ እንደሚጮህባት፣ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታዬ ነው እንዳላለ፣ በአሜሪካ ከተሞች መሬት ላይ እንደማይንደባለልባት ፈፅሞ ጥርጣሬና ቅንጣት ግምት አልነበረውም።

የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘመናት አሳንሶ ከማየት የሚጀምረው የጁንታው እቡይነት፣ እብሪተኝነትና ትዕቢት እንዲህ እንደሚሟሽሽም ፈፅሞም አልገመተም። ግን ኢትዮዽያውያን ታሪኩን ቀየሩት። መብረቃዊ ጥቃት ፈፀምኩ ባለበት አፉ መብረቅ ሆኑበት፣ መብረቅም አወረዱበት። ያንን አብጦ የከረመ እብሪት እንደ ጎማም አተነፈሱት። አድኑኝ ብሎ ይጨህ ዘንድ፣ ይንከባለልም እንደሁ አስገደዱት። ጁንታው እንዳልቦረቀ ሁሉ፣ አጎነበሰ። ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እግዚኦ አለ። እድሜ ልኩን በስሙ እየነገደበት ላለው የትግራይ ህዝብ በእኔ ተማመን ሲል እንዳልከረመ፣ ምቱና ወቀራው ቢያይልበት ድል በእጄ ናት ሲልም ሰበከ። ትግራይ ዋሻዎች ሆኖ አዲስ አበባ አፋፍ ነኝ፣ በሳምንት ባልገባ ውርድ ከራሴ ሲልም ፎከረ፤ ህዝቡን እያስጨረሰ ፈቅ በማይለው ሙት አስተሳሰቡ ጁንታው ባለበት ቀረ።

አሸባሪው ወያኔ ትህነግ አቅሙንም፣ ልቡ ያለችበት የቀነጨረ አካሉንም ፈፅሞ አውቆት አያውቅም፣ ድንፋታና እብሪቱን፣ የስነ ልቦና ጦርነቱን ከሰላሳ በዘለቀ የአገዛዝ ዘመኑ ተለማምዶታል። ሞቶም እንኳ ማቅራራቱን ያውቅበታል። የቀብር ውስጥ ፉከራና ቀረርቶው ጉሮሮው ውስጥ ልትሰነቀር መሆኑን እንኳን ፈፅሞ አልተረዳውም። ህዝቡን ማስጨረሱንም ከቁብ አልቆጠረውም። የጀመረው ሽብርና እልቂት የቆመ እለት እንደሚበላም ያውቃል።

አጥፍቶ መጥፋትን የመረጠውና በዚህ ክፉ ህልምና ቅዥቱ ላይ የተቸነከረው ለዚሁ ነው። ከሞት ግን የሚያድነው የለም። የጁንታው ልብ አለቅጥ አብጧል፤ መፈንዳቱም አይቀርም፤ ይልቅ አሸባሪው ወያኔ ትህነግ ያለው ብቸኛ ተስፋና መጨረሻ፣ ያቺ ሰይጣናዊ እጁ የተሰነዘረችበትን ቀንና ፣ ሰይጣናዊ ሀሳቡን ያፈለቀውን ጭንቅላት እየኮነነ ‹‹ዋ! ያቺ ዕለት የተረገመች ትሁን!›› ማለት ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም