በሴቶች ጥቃትና እኩልነት ዙሪያ የተሰሩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል

118

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20/2014 (ኢዜአ) በሴቶች ጥቃትና እኩልነት ዙሪያ የተሰሩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ለሕብረተሰቡ ግንዛቤን በማስጨበጥ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ በሴቶች ጥቃትና እኩልነት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አምስት የፊልም ስራዎችንና ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።

'ሔርሜላ'፣ 'ፍሬ'፣ 'ድፍረት'፣ 'እምነት' እና 'የሎሚሽታ' የተሰኙ ፊልሞች በዘርፉ ብዙሃንን ያስተማሩና ጊዜ የማይሽራቸው ሆነው ለተመልካች በመድረሳቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ከአምስቱ ፊልሞች መካከል ደግሞ 'ሔርሜላ" እና 'ፍሬ' የተሰኙት ኪነጥበብ ስራዎች ተመርጠው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የማህበሩ ዳይሬክተር ሌንሳ ቢየና በዚህን ወቅት እንዳሉት የሴቶች ጥቃት እና እኩልነት ላይ የተሻሉ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ከጉዳዩ ውስብስብነት አንጻር ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡

የሴቶች ጥቃት እንደየ አካባቢው ባህል፣ ወግና ልማድ የሚፈጸም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ በቀላሉ እንዳይፈታ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በፊልም ተደግፈው የሚሰሩ የኪነጥበብ ስራዎች ጥቂት ቢሆኑም በቀላሉ ማህበረሰቡ ውስጥ ሰርጾ የመግባት አቅም እንዳላቸውም አንስተዋል።

የፊልም ስራዎቹ በቀላሉ ግንዛቤን የሚፈጥሩና ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም መሰል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

እውቅና ያገኙት ፊልሞች በሴቶች ጥቃትና እኩልነት አስተማሪ ስራዎችን በመስራት ማህበረሰቡን በብዙ ያነቃቁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ የቦርድ አባል ወይዘሪት ማህሌት ፍጹም ናቸው።

በቀጣይ የኪነጥበብ ስራዎችን እንደ አንድ ግንዛቤ የማስጨበጫ ዘዴ አድርጎ የመጠቀሙ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

እውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው የፊልም ባለሙያዎች በበኩላቸው የኪነጥበብ ስራን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማስተማርና በማንቃት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

እውቅናና ሽልማቱ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ይበልጥ እንዲሰሩ እንዳነሳሳቸውም ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ላለፉት 27 ዓመታት ነፃ የሕግ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ በዘርፉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም