በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን የተያዙ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት ተዘጋጅተናል

462

ባሀር ዳር፤ ጥቅምት 19/2014(ኢዜአ) ወደ ግንባር በመዝመት በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን የተያዙ አካባቢዎችን ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ነፃ ለማውጣት መዘጋጀታቸውን በዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወጣቶች አስታወቁ።

ከዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ተፈናቅለው በዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወጣቶች የማነቃቂያ ስልጠና በባህር ዳር ከተማ ተሰጥቷል።

በስልጠናው የተሳተፈው ወጣት ሙላት አለማው፤  የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በፈፀመው ወረራ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው ቢወጡም በባህር ዳር እና አካባቢው ህዝብ ተገቢውን ድጋፍ እያገኙ እንደሆነ ተናግሯል።

ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ ወራሪውን ቡድን በመፋለም የያዛቸውን አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት መነሳሳቱንም ገልጿል።

“በመጠለያ ጣቢያ ሆነን በሚሰፈር እህል የሚመጣ ነፃነትና ክብር ስለማይኖር የክተት ጥሪውን ተቀብየ ለመዝመት ዝግጁ ነኝ” በማለት፤ ለዚህም አስፈላጊውን ትጥቅና ስንቅ እንዲዘጋጅ ጠይቋል።ሌላው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኘው ወጣት ዘላለም መልካሙ በበኩሉ፤ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ቡድን ለሰው ልጅ የማይራራ በመሆኑ ፊት ለፊት ለመፋለም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

እኔን ጨምሮ በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ወጣቶች በአንድነት በአሸባሪው ወራሪ የህወሓት ቡድን የተያዙ አካባቢዎችን ከመከላከያና ልዩ ሃይል ጋር በመሆን ነፃ ማውጣት ይኖርብናል ብሏል።

መከፋፈልንና መለያየትን አሸባሪው ቡድን ትልቅ መሳሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት መሆኑን ጠቅሶ፤ ወጣቱ ይህንን በመረዳትም አንድነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ገልጿል።

በክልሉ ላጋጠመው ፈተና ወጣቱ ”እኛ ለእኛ መፍትሄ ነን” በሚል መንፈስ  መንቀሳቀስ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው።

አሸባሪው  የህወሃት ቡድን የፈፀመውን ወረራ መክቶ ለመደምሰስ ወጣቱ በተደራጀ እና በቁጭት መነሳት እንደሚኖርበትም ነው የገለጹት።

የአሸባሪው ቡድን ለሰው ልጅ እንደማይራራ በማይካድራ፣ ጭናና ቆቦ የፈፀመው ድርጊት ትልቅ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።


የክልሉ ወጣት ነፃነት የሚያገኘው መስዕዋትነት በመክፈል መሆኑን ተገንዝቦ በመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ መቀላቀል እንዳለበትም  አስገንዝበዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በፈፀመው ወረራ ምክንያት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች  ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያና ከመጠለያ ውጭ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወይዘሮ እታገኘሁ እንዳሉት፤ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ እየተደረገ ነው።

የተፈናቃዮችን ችግር ለማቃለል  ወጣቱ በተደራጀ አግባብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የተወረሩ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት እንደሚጠበቅበትም ነው ያመለከቱት። 


በማነቃቂያው ስልጠና ማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት በዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወጣቶችና የሚመለከታቸው የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።