የእንጦጦ የአጤ ምኒልክ ቤተ-መንግስት በወቅቱ ባለመታደሱ አደጋዎች ተጋርጠውበታል

217
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 እንጦጦ የሚገኘው የዳግማዊ አጤ ምኒልክ ቤተ-መንግስት በወቅቱ ባለመታደሱ አደጋዎች እንደተጋረጡበት ተገለፀ። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማደስ ዝግጁ ነኝ ብሏል። የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የልደት በዓል በእንጦጦ የምኒልክ ቤተ-መንግስት አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል። ቤተ-መንግስቱ በወቅቱ እድሳት ስላልተደረገለት የመበላሸትና የመርገፍ አደጋ ይታይበታል፤ ህልውናው አደጋ ውስጥ መሆኑ እንዳሳዘናቸው በበዓሉ የተገኙ ታዳሚዎች ተናግረዋል። ቅርሱን መንከባከብ ታሪክን ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር በቱሪዝም ትልቅ ገቢ ለማስገኘትም ትኩረት ባለማግኘቱ አደጋ ውስጥ ወድቋል ነው ያሉት። አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዳለው ባለድርሻ አካላት ታሪክን ለትውልድ ለማስተለላፍ ቅርሱን የመጠበቅና የመንከባከብ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም በበኩላቸው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚያኮራ ገድል የፈጸሙ ጀግና መሆናቸውን ጠቅሰው የሰሩትን ታሪክና በዘመናቸው የነበረውን ቤተ-መንግስት ያለመጠበቅ የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል ብለዋል። ፖለቲከኛው ዶክተር ካሳ ከበደም እንዲሁ ባለፉት ስርዓቶች ለቅርሱ ተገቢው እንክብካቤ ባለመደረጉ አሁን እየታየ ላለው ችግር መጋለጡን ይናገራሉ። ለዚህም በየጊዜው ለቅርሱን በባለቤትነት የሚከታተል አካል ሊመሰረት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ቤተ-መንግስቱን ለማደስ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጥበብና እውቀት ያስፈልጋል ያለው የአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አርቲስት ነብዩ ባዬ ቢሮው በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። የዳግማዊ አጤ ምኒልክ 174ኛ እንዲሁም የእቴጌ ጣይቱ ብጡል 178ኛ ዓመት የልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም