በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአማራ ልማት ማህበር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

61

ጥቅምት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአማራ ልማት ማህበር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚልዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ፣ የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎች፣ ከባለሀብቶች እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶ የተሰባሰበ ሲሆን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ተብሏል።

የቂርቆስ ክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ ድጋፉ 15 ቀናት ባልሞላ ጊዜ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

"ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበር እና መደጋገፍን የሚጠይቅ በመሆኑ የተጎዱትን መርዳት እና መደገፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ጌትነት አለሙ፤ ማህበሩ በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚልዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ከ10 ሚልዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከሰብአዊ ድጋፉ በተጨማሪ በአሸባሪው ቡድን የፈረሱ ተቋማትን መልሶ ለመስራት ለሚደረገው ጥረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአማራ ልማት ማህበር ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀሚድ አህመድ፤ ማህበሩ ከዚህ ቀደም ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ "ወደ ፊትም ተባብረንና ተጋግዘን የገጠመንን ችግር እናለፈዋለን" ብለዋል።

በመርሀ ግብሩ ማጠናቀቂያ ድጋፉን ላሰባሰቡ አካላት የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም