በደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል

510

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) በደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳሰበ።

አስተዳደሩ ሁለተኛውን የሳይበር ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከመንግስት የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተውጣጡ የአይሲቲና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳሬክተር አንተነህ ተስፍዬ፤ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት አለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳይበር ተጋላጭነት እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

በአውሮፓዊያኑ 2020 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ዓለም በሳይበር ጥቃት ምክንያት በዓመቱ 2 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር አጥታለች።

የሳይበር ጥቃቱ በዚሁ ከቀጠለ በ2025 ዓለም 6 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችል ገቢ ልታጣ ትችላለች የሚል ግምት መኖሩንም ምክትል ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም አሰራሮች ወደ ዲጂታል እየተቀየሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች እየተበራከቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የመንግስት የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።

የተቋማቱ ማህበራዊ ትስስር ገፆችና ሌሎች አገልግሎቶች የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጠንካራ የይለፍ ቃል አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ ሲሉም መክረዋል።

የሳይበር ጥቃት የደህንነት መረጃዎችን በመመንተፍ አገርን አደጋ ላይ ስለሚጥል ጥንቃቄውን ማጥበቅ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ መከላከያና ሌሎች የመንግሥት የጸጥታና የደህንነትና ተቋማት የተውጣጡ ሙያተኞች በስልጠናው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።