ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ በመዝረፍ ወንጀል የፈጸሙ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

269

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ በመዝረፍ ወንጀል የፈፀሙ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የተደራጁ ዘራፊዎች ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኝ የሕብረት ባንክ ሲኤምሲ ቅርጫፍ ከአንድ የባንኩ የጥበቃ ሰራተኛ ጋር በመመሣጠር ሌሊት ላይ ዘረፋ መፈጸማቸው ነው የተገለጸው።

በእለቱ አንደኛውን የባንኩ የጥበቃ ሰራተኛ በመደብደብ፣ በማፈን እና እጅና እግሩን በማሰር የዘረፋ ወንጀሉን መፈፀማቸውን መግለጫው አመልክቷል።

በእለቱ 2 ሚሊየን 100 ሺህ 969 ብር፣ 900 የአሜሪካ ዶላር፣ 65 ድርሃም እንዲሁም 8 ሞባይሎችን የዘረፉት ሶሰት ግለሰቦች በአጭር ሰአታት ውስጥ ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ባደረጉት ክትትል የወንጀሉ ተሳታፊዎች ከዘረፉት ገንዘብና ለወንጀል ድርጊት ከተጠቀሙበት አንድ ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

የሕብረት ባንክ የሲኤምሲ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አቤኔዘር ጥሩነህ፤ የፖሊስ አባላት ወንጀሉ በተፈፀመ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋላቸው አመስግነዋል።

የገርጂ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ካሳሁን ነገዎ፤ የፋይናንስ ተቋማት የጥበቃ ስርዓትን ማሻሻል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።