የሃይማኖት ተቋማት ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁ ተግባራት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል

76

ጥቅምት 18/2021 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁና አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ አተኩረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስገነዘበ።

ባካሄደው 10ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤው በ2013 የእቅድ አፈፃፀምና የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ መክሯል።

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስና የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፤ የሃይማኖት ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ ሠላም በመስበክ መልዕክቶችን በአደባባይ ጭምር ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት በተለይም በሠላም እሴት ግንባታ፣ በስነ-ምግባርና የሞራል ግንባታ ላይ በማተኮር ውይይቶችና ስልጠናዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

አገርን ማልማት ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ቤተ-እምነቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርና ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ መሳተፋቸውንም አውስተዋል።

የሃይማኖት ተቋማቱ በቀጣይም አንድነትን በሚያጠናክሩና ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁ እንዲሁም የአገርን ልማት በሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ ጉባኤው በ2013 ዓ.ም በርካታ የሠላምና የልማት ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሸባሪው ህወሓት ተገዳ የገባችበትን የህልውና ዘመቻ እንድታሸንፍ ከፀሎት እስከ አብሮነት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ እየታየ ላለው ሠላምና አብሮነት የሁሉም ቤተእምነቶች ሚና የላቀ እንደነበር ጠቅሰው ለአገር መከላከያና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ለሠራዊቱ ሲያደርጉት የቆዩትን ድጋፍ አሁንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የግብረ-ገብነት ትምህርት ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር ለማነፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸው በቀጣይም በልዩ ትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም