አሸባሪዎቹን ሸኔ እና ሕወሓት ሲደግፉ የነበሩ 88 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

110

አዳማ፤ጥቅምት 18/2014(ኢዜአ) በአዳማ ከተማና አካባቢዋ ለአሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 88 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ከበደ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት አሸባሪዎቹን በፋይናንስ፣ በቁሳቁስና በመረጃ በመደገፍ ሀገር ለማፍረስ በሚያደርጉት እቅስቃሴ ውስጥ መሳተፋቸውን በጥናት ተለይቶ ነው።

የፀጥታ ሃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባደረገው እንቅስቃሴ ሰሞኑን 88 ተጠርጣሪዎችን በመቆጣጠር ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

አዳማ  በቀን  ከ100ሺህ ህዝብ በላይ የሚወጣባትና የሚገባባት ከተማ ናት ያሉት ኮማንደር ከበደ፤ ሰርጎ ገቦች አጋጣሚውን ተጠቅመው ሾልኮው እንዳይገቡ የፀጥታ አካላት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች 24 ሰዓት ክትትል፣ ቁጥጥርና ፍተሻ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በዚህም ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ኮማንደሩ፤ ስምንት ክላንሽኮቭ ጠብመንጃዎች፣ 18 ሽጉጦችና የተለያዩ ኋላቀር የጦር መሳሪያዎች 1ሺህ ከሚጠጉ መሰል ተተኳሽ ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አመልክተዋል።

"ስለ ውያኔና ሸኔ ድርጊት ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል፤ አሸባሪዎቹን ለመደምሰስ እየተካሄደ ባለው ትግል ለመሳተፍ  ከ19ሺህ በላይ የከተማዋ ወጣቶችና ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ወታዳራዊ ስልጠና ወስደው የአካባቢውን ሰላም ከማስፈን ባለፈ ግንባር ድረስ ለመዝመት በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል።

ልዩ ሃይሉ፣ መደበኛ ፖሊስና ሚሊሻ በምዕራብ ኦሮሚያ ሸኔን እየተፋለመ ከመሆኑም ባለፈ ህብረተሰቡን በማስተባበር በሰሜን ግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ሠራዊት ያልተቋረጠ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ወጣቶች አሸባሪውን ሕወሓት በሀገር ላይ በፈፀመው ክህደት ቁጭት ውስጥ በመግባት መከላከያና የክልሉን ልዩ ሃይል እየተቀላቀሉ ነው ብለዋል።

በዚህም አሸባሪውን ሕወሓት እስከ መጨረሻው ለመቅበር ዝግጁ ነን ያሉት ኮማንደር ከበደ፤ ህዝቡ ወራሪውን ሃይል ለመደምሰስ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሞራል እንዲሁም ግንባር ድረስ በመሄድ ስንቅ በማቀበል እያደረገ ያለውን ርብርብ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተለይም የከተማዋ ፀጥታ አካላት፣ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስና ሚሊሻ በ149 ተንቀሳቀሽ የክትትልና ቁጥጥር ቦታዎች እንዲሁም በ29 ቋሚ የጥበቃ ኬላዎችን በማደረጃት የአሸባሪዎቹ ሸኔና  ሕወሓት ተላላኪዎችና ሰርጎ ገቦችን እንቅስቃሴ የማምከን ስራ እየተካሄደ ነው መሆኑንም ነው ኮማንደር ከበደ የጠቀሱት።

በዚህም የጥፋት ሃይሉ የከተማዋን ሰላም የማወክ ፍላጎትና ምኞት ህልም ሆኖ እንዲቀር ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ የጥፋት ተላላኪዎች በሆቴሎችና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች ጭምር ሊኖራቸው የሚችለውን እንቅስቃሴ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም