የኢትዮጵያ ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል

173

ጥቅምት 18/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ቢሊዮን ሊትር መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

"ቀዳሚና ሁሉን አቀፍ የዶሮ እና እንስሳት ሃብት ቴክኖሎጂ ግብዓትና መፍትሄዎቻቸው" ዓለም አቀፍ የንግድ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በእንስሳት እርባታ ላይ ጥገኛ ነው።

የእንስሳት እርባታ ግብርና ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ካለው አስተዋጽኦ 45 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል።

የዘርፉ የአመራረት ስርዓት ውስን በሆነ የገበያ አቅጣጫ መተዳደሪያ ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል።

የእንስሳት እርባታው ለኅብረተሰቡ የሚያበረክተው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጥቅሞች እንዲጨምር ባለድርሻ አካላት የቁጥጥር ማዕቀፎችን፣ ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንትን መደገፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት በፍጥነት እየጨመረ ቢሆንም ከአገር ውስጥ የምርት እድገቱ ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገሪቷ የወተት ምርት መጠን ከ4 ቢሊዮን ሊትር በዓመት ወደ 7 ቢሊዮን ሊትር ማደጉን ተናግረዋል።

ዶክተር ፍቅሩ መንግስት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ማበረታቻዎች ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል የተቋቋሙ የእንስሳት እርባታ አምራቾች የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉና እሴት ጨምረው ራሳቸውንና አገራቸውን በመጥቀም የአፍሪካን ገበያ ጭምር እንዲያገለግሉ ያበረታታል ነው ያሉት።

የንግድ ትርዒቱ በሁሉም የእንስሳት እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ምርታማነትን በሚያሻሽሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲወያዩና ግብይት እንዲፈጥሩ መድረክ ይፈጥራል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ በሁሉም የእንስሳት ሃብት የገበያ ሰንሰለቶች ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ይተዋወቃሉ።

የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲሁም የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት መሰረታቸውን በሰባት አገራት ያደረጉ ድርጅቶች እንደሚሳተፉም ተመላክቷል።

ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት አውደ ርዕዮች ለዶሮ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለወተት እና ስጋ እንዲሁም ለእንስሳት የጤና እድገት አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተገልጿል።

የንግድ ትርዒቱ በኮቪድ-19 ሳቢያ ተቀዛቅዞ የቆየውን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የተዘጋጀ ነው።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው አውደ ርዕይ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ድርጅቶችና አምራቾች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም