በሲዳማ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 3 ሺህ 943 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሐዋሳ ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 3 ሺህ 943 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ማዘንጊያ ሾንቶካ ለኢዜአ እንደገለጹት የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

የንግድ ድርጅቶቹ ከሕገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ምርትን በመሰወርና በማን አለብኝነት የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆነው በመገኘታቸው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተወሰደው እርምጃ 2 ሺህ 160  የንግድ ተቋማት ማሸግና ስምንት ተቋማት ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ሌሎች 1 ሺህ 775 የንግድ ተቋማት ደግሞ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ቢሮው ምርትን በአምራቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለገበያ ለማቅረብ የሚረዳ ወጥ አሰራር በመዘርጋት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሐዋሳ ከተማ በግል ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ቤተልደታ አብርሃም መንግሥት አግባብ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩና ህገወጥ ደላሎችን በመቆጣጠር ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

"አሸባሪው ህወሃት ቡድን የታወጀውን ጦርነትና የምዕራባዊያንን ጫና ለመመከት ርብርብ እየተደረገ ባለበት ወቅት መተሳሰብን ወደ ጎን ትተው የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ራስ ወዳድ ነጋዴዎች ላይ እየተደረገ ያለው ቁጥጥር መጠናከር አለበት" ብለዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪና በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ መስከረም ሙሉጌታ በበኩላቸው በየዕለቱ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ እንዳማረራቸው ገልጸዋል።

በተለይ የምግብ ዘይት ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የፋብሪካ ምርቶች ላይ በየዕለቱ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

በሐዋሳ ከተማ ሰሞኑን በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ መሻሻል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአቅርቦትና ቁጥጥር ላይ ሕዝብን በማሳተፍ እንዲሰራ ጠይቀዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም