ማህበሩ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶችና መድሀኒቶችን ለነገሌ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

80

ነገሌ ጥቅምት 18/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶችና መድሀኒቶችን ለነገሌ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ።

በማህበሩ የነገሌ የቅርንጫፉ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮሐንስ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ የህክምና መርጃ ቁሳቁስ እጥረት እንዳለበት በመግለጽ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ድጋፉ ተደርጓል።

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ የድንገተኛ ህክምና መርጃ መድሀኒቶች፣ የኮሮና መከላከያዎች፣ የሙቀት መለኪያና ማዳመጫ መሳሪያዎችና 50 ሺህ ሊትር ውሃ መያዝ የሚችል የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ማህበሩ በዞኑ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ለ48 የአርብቶ አደር ቤተሰብ አባላት የምግብ እህል በማከፋፈል ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የህክምና ቁሳቁሱን የተረከቡት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ቦሩ ጃርሶ ድጋፉ የሆስፒታሉን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ ከአሁን በፊት 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድሐኒቶች፣  አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎችንና ሌሎች የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን ለሆስፒታሉ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ማህበር ለዜጎች ተደራሽ በመሆን የጀመረውን የሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተሩ ጠይቀዋል።

የነገሌ ሆስፒታል በአማካኝ በየቀኑ ከ1ሺህ እስከ 1ሺህ 200 ለሚሆኑ ተመላላሽና ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም