ልጅ ወልዶ መሳምና በሰላም አሳድጎ ለወግ ማብቃት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው

73

ሰመራ፤ ጥቅምት 17 /2014 (ኢዜአ) ''ልጅ ወልዶ መሳምና በሰላም አሳድጎ ለወግ ማድረስ የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው" ሲሉ አሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት በህልውና ዘመቻ እየተሳተፉ ያሉ የዘማች ባለቤት ወይዘሮ ሀስና ኢብራሂም ተናገሩ።

ሶስት ልጆችን በሰላም የተገላገሉት ወይዘሮ ሀስና ባለቤታቸው ለሀገር ሰላም በሚደረግ ተጋድሎ የድርሻቸውን እየተወጡ በመሆናቸው ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል።

በሀገር ህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ያሉ የዘማች ባለቤት ወይዘሮ ሀስና ኢብራሂም በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ በሚገኘው ባርባራ ሜይ የእናቶች ሆስፒታል ትናንት ሶስት ልጆችን በሰላም ተገላግለዋል።

በሆስፒታሉ ሶሰት ልጆችን በሰላም የተገላገሉት ወይዘሮ ሀስና ኢብራሂም ከአሁን በፊት ስድስት ልጆች መውለዳቸውን አስታወሰው፤ እንደ አሁኑ መንታ የመውለድ አጋጣሚ አንዳልነበራቸው ጠቁመዋል።

ባለቤታቸው የህወሓት የሽብር ቡድን የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ ሃገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በአካባቢ ሚሊሻነት ግንባር ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም፤ ሶስት ልጆችን በሰላም የመገላገላቸው አጋጣሚ የፈጣሪ በረከት በመሆኑ በደስታ እንደተቀበሉት ተናግረዋል።

''ልጅ ወልዶ መሳምና በሰላም አሳድጎ ለደረጃ ማድረስ የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው'' ያሉት ወይዘሮ ሀስና፤ ባለቤታቸው ለሀገር ሰላም በሚደረግ ተጋድሎ የድርሻቸውን እየተወጡ በመሆናቸው ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸው አመልክተዋል።

አሁን ላይ በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው በየቦታው ተሰደው እንደሚገኙም ነው ያስታወቁት።

ይሁን እንጅ ያለምንም የከፋ ችግር ሶሰት ልጆችን በሰላም በመገላገላቸው ጦርነቱ ከፈጠረባቸው ሀዘንና ጭንቀት እንዲጽናኑ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።

የሆስፒታሉ ሰራተኞችና ታካሚዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ እያደረጉላቸው ያለው ድጋፍና እንክብካቤ በቤተሰቦቻቸው መሃል ያሉ ያህል እንዲሰማቸው ማድረጉንም ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ አዋላጅ ነርስ ሲስተር ዘሃራ መሐመድ ክስተቱን አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለጹት ወይዘሮ ሀስና ከወር በፊት ለቅድመ-ወሊድ ክትትል ከጭፍራ ወረዳ አሴኮማ ቀበሌ ወደ ሆስፓታሉ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።

ጽንሱ ሶስት መሆኑ ባይታወቅም በወቅቱ በተደረገ የህክምና ምርመራ መንታ እንደሆነ የሚያሳይ እንደነበር ገልጸዋል።

የመጡበት አካባቢም ርቀት ስለነበረው በወሊድ ወቅት ሊፈጠር በሚችል አደጋ እንዳይጋለጡ በሆስፒታሉ የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ የሁሉም ህክምና ባለሙያዎች ሃሳብ በመሆኑ ነፍሰ ጡሯን በማግባባት ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ መደረጉን ጠቁመዋል።

በአሀኑ ሰዓት ወይዘሮ ሀስናም ሆነ ሶሰት ጨቅላ ህጻናቱ የህክምና እንከብካቤና ድጋፍ እየተደረገላቸው በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት ወደ አካባቢያቸው መመለስ የማያስችል የጸጥታ ችግር ያለበት በመሆኑ የጸጥታው ችግር ተፈቶ ወደ አካባቢያቸው መመለስ እስከሚችሉ ድረስ በሆስፓታሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም