የፌዴራል ስርዓቱ በአግባቡ እንዲተገበር የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ተቋማት ገለልተኛ መሆን አለባቸው--ኦፌኮ

80
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 የፌዴራል ስርዓቱ በአግባቡ እንዲተገበር የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ተቋማት ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ገለጹ። ፓርቲው ዛሬ በፌዴራላዊ ስርዓት እና በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሄዷል። የህግ የበላይነትን ማክበር የዲሞክራሲ ተቋማትን ለአብነትም ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት የመሳሰሉት ገለልተኛ በማድረግ የፌዴራል ስርዓቱ በአግባቡ እንዲተገበር ያደርጋል ብለዋል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማበረታታት፣ የስልጣን ክፍፍል፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መጠናከር፣ ሚዲያ እና ሌሎች ተቋማት በእኩልነት የኢትዮጵያ ህዝብን በአግባቡ በሚያገለግሉበት መልኩ መደራጀት አለባቸው ብለዋል። እነዚህ ተቋማት ገለልተኛ ባልሆኑበትና በመንግስት ተጽእኖ ስር ባሉበት ሁኔታ ስርዓቱን ማራመድ አይቻልም ሲሉ ጠቁመዋል። በአንድ አንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን የህግ-የበላይነትን በማስከበር መንግስት የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት ሲሉም ዶክተር መረራ ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ተሰማ ተኣ እንዳሉት "ከባለፈው ታሪክ ስህተት በመማር አሁን በአንድነት ወደፊት መጓዝ ያስፈልጋል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለአፍሪካ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉንም ልዩነቶቻችንን በማክበር ዘላቂ ሰላም በማስፈን አብሮነታችንን ማጠናከር አለብን ሲሉም ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ አሁን የሚታየውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መንግስት በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮች እንዲቆሙ እና የተገኘው የለውጥ ጉዞ እንዳይቀለበስ የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት ብለዋል። የመድረኩ ተሳተፉዎ በሰጡት አስተያየት በህገ-መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የዜጎች ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር አለባቸው ብለዋል። ህዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ የማሳደግ ሁኔታዎች አሁን ከተጀመረው በላይም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት። በህዝቦች መካከል ግጭቶችንና መከፋፈልን የሚፈጥሩ ሰዎችን ለህግ የማቅረብ ስራዎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውና ህዝቡም እነዚህን አካላት የማጋለጥ ስራ መስራት አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም