ለበጎ ስራ በአርቲስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል በተካሄደው ውድድር ድጋፍ ተገኘ

84

ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለወሎ ተፈናቃዮች የገቢ ማሰባሰቢያ ታስቦ በአርቲስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል በተካሄደው ውድድር የገንዘብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ።
ውድድሩ በአዲስ አበባ አበበ ቢቄላ ስታዲየም በኢቢኤስ፣ ኢቢሲ፣ ብስራት ኤፍ ኤም እና አርቲስቶች መካከል ሲካሔድ ቆይቷል፡፡

በውድድሩ ሂደት አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ከወሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች ዘይት፣ ፓስታና ማካሮኒ እንዲሁም የገንዘብና አልባሳት ማሰባሰብ የተደረገ ሲሆን በዛሬው እለትም ተጠናቋል።

የሃሳቡ አመንጭ እና የዝግጅቱ አስተባባሪ ጋዜጠኛ ዘላለም ሙላቱ እንደገለጸው የእግር ኳስ ጨታው አላማ በአማራ ክልል ወሎ አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡

በውድድሩ ሂደትም የገንዘብ፣ አልባሳትና ለምግብ ፍጆታ የሚውል ድጋፍ ተገኝቷል ብሏል ጋዜጠኛ ዘላለም።

የወሎ ቤተ-አምሃራ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና የዝግጅቱ አስተባባሪ ወጣት አራጋው ሲሳይ፤  የውድድሩ ዋና አላማ በወሎ እና አካባቢው ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ገቢ ለማሰባሰብ ነው።

ኢትዮጵያዊያን በመረዳዳትና መተጋገዝ ባህላችን እንታወቃለን ያለው  አራጋው በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ሁላችንም እንድረስላቸው ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በወሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች የድርሻዬን ለመወጣት በውድድሩ ላይ አርቲስቶችን ወክየ ተሳትፌያለሁ ያለው ደግሞ አርቲስት ብርሃኑ ገረመው ነው።

የኢቢሲው ጋዜጠኛ ፈረደ ጭብሳ በበኩሉ “እንደ ሀገር የገጠመንን ችግር ተባብረን እና ተረዳድተን ልናስወግደው ይገባል” ብሏል፡፡

ችግር በማናችንም ላይ ሊደርስ ይችላል ያለው ፈረደ አሁን በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ልንረባረብና በቶሎ ልንደርስላቸው ይገባል ብሏል።