የአሸባሪውን ቀብር በወሎ ምድር ላይ እናደርጋለን---ወደ ወሎ ግንባር የዘመቱ ወጣቶች

124

ደሴ ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) ''የአሸባሪውን ህወሓት ወራሪ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ደምስሰን የመጨረሻ ቀብሩን በወሎ ምድር እናደርጋለን'' ሲሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ወሎ ግንባር የዘመቱ ወጣቶች ገለጹ፡፡
 የሀገሪቱ  ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች  በጥፋት ተግባር የተሰማራውን የህወሓት ወራሪ ሀይል ለመፋለም በወሎ ግንባር እየዘመቱ ነው፡፡

ከጎንደር ከተማ የመጣው ወጣት ሙላት አድነው ለኢዜአ እንደገለጸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ወግኖ እየሰራ ያለውን የህወሀት ቡድን ተባብሮ መቅበር ሀገራዊ ሀላፊነት ነው።

ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች በንጹሀን ላይ ዘግናኝ ግፎችን መፈጸሙን አስታውሶ፣ "በጠንካራ ክንዳችን የቡድኑን የመጨረሻ ቀብር ወሎ ላይ እናደርጋለን" ብሏል።

እንደ ወጣቱ ገለጻ ወደ ወሎ ግንባር የመጣው ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይሉና ሌሎች የፀጥታ አባላት ጋር ተቀናጅቶ የህወሓትን የሽብር ቡድን ግብአተ መሬት ለመፈጸም ነው።

"እንደ ጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕት ከፍለን ኢትዮጵያን ከጥፋት ቡድኑ ነጻ እናወጣለን" ብሏል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምጣቱን የገለጸው ወጣት ኢንጂነር ይበልጣል ታደሰ በበኩሉ እንዳለው የሀገር ነቀርሳ የሆነው የሽብር ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ካላጠፋ ህዝብ በሰላም አይኖርም።

"የጥፋት ቡድኑ በፈጸመው ዘግናኝና አስነዋሪ ግፍ ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው፣ በጀምላ ተገድለውና ተዘርፈው አዲስ አበባ መቀመጥ አልቻልኩም" ሲልም ወጣቱ ተናግሯል።

የቡድኑን ግብዓት ቀብር ወሎ ምድር ላይ በመፈጸም ህዝብና ሀገሩን ነጻ ለማውጣት ለህይወቱ ሳይሳሳ በወሎ ግንባር መሰለፉን ተናግሯል፡፡

"የወሎ ወጣት በህወሓት የውሸት ወሬ ተረብሾ መሸሽ ሳይሆን የጀመረውን የደጀንነት ተግባር በማጠናከር ቡድኑን በመቅበር የአባቶቹን ታሪክ ማስቀጠል ይኖርበታል" ብሏል፡፡

"ቡድኑ አድማሱን ሳያሰፋ ከወሎ ወንድሞቻችን ጋር ተቀናጅተን ባለበት ለመቅበር ቆርጠን መጥተናል" ያለው ወጣቱ አሸባሪውን በግንባር ለመፋለም መዘጋጀቱን ገልጿል።  

ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን ለማውደም የቋመጠውን ዘራፊ ቡድን በቅንጅት መመከት ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይነሳ እድርጎ መምታት እንደሚገባ ተናግሯል።

"ጀግኖች አባቶች በደምና አጥንታቸው ያቆዩንን ሉዓላዊት ሀገር እኛ እያለን ብናስደፍር አጥንታቸው ይወጋናል፤ በታሪክም እንወቀሳለን" ያለው ደግሞ ከጎጃም አካባቢ የመጣው ወጣት ልጃለም ባለው ነው፡፡

በውሸት ወሬ ያደገውን የህወሓት የሽብር ቡድን በቅንጅት በመደምሰስ ቀብሩን በወሎ ተራሮች ላይ  እውን ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱን ተናግሯል።

እንደ ወጣቱ ገለጻ የወሎ ተራሮችን አልፎ ወደ መሃል ሀገር ለመግባት እያሰፈሰፈ ያለውን ቡድን ለማጥፋት የኢትዮጵያ ወጣት የጀመረውን አንድነትና ተሳትፎ ማጠናከር ይኖርበታል።

"ከመከላከያ ሠራዊቱና ከወሎ ህዝብ ጋር በመተባበር የቡድኑን ዕድሜ ለማሳጠርና የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማብሰር እስከ ህይወት መስዋት እከፍላለሁ" ሲልም ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

የኢዜአ ሪፖርተር በወሎ ግንባር ተገኝቶ እንደተመለከተው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶችና የፀጥታ አባላት ጠላትን ለመፋለም በግንባሩ እየዘመቱ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም