ኢትዮጵውያን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ድል አድራጊዎች ናቸው

77

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ድል አድራጊዎች መሆናቸውን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊን ከጥንት ጀምሮ የአደዋ ድል ታሪክና ሌሎች አስቸጋሪ መሰናክሎችን በአሸናፊነት በማለፍ የካበተ ልምድና አስደናቂ ታሪክ እንዳላቸው በርካቶች ይናገራሉ።

በእንግሊዝ ለንደን የሚኖሩት አቶ ፋሪስ ሙሀመድ፤ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በብዙ ፈተናዎች ድል አድራጊዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።

በአድዋ  ጦርነት ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀን ወራሪ ሃይል ድል በመንሳት ኢትዮጵያ የዓለም የጥቁር ህዝቦች የድል አድራጊነት ተምሳሌት መሆኗን አስታውሰዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ከውጭም ይሁን ከውስጥ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሰለፉ ሃይሎችን ከማሸነፍ የሚያግዳት ምድራዊ ሃይል የለም ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብርና ለሰንደቃቸው ልእልና በጋራ መቆማቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን አንስተዋል።

የኖርዌይ ነዋሪዋ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ዓለማየሁ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ተቋቁማ አሸናፊ እንደምትሆን ማናችንም አንጠራጠርም ብለዋል።

ለዚህም ሁላችንም የቀደሙት አያቶቻችንን ታሪክ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

የህወሃት አሸባሪ ቡድንና ተቀጣሪዎቹ የሚያናፍሱትን የፈጠራ ወሬ በማምከን እንዲሁም በሁሉም አውደ ግንባሮች በመሰለፍ አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ዳያስፖራው ከዚህ በፊት ለአገር እድገት ሲያደርግ የነበረውን መልካም ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያን ከችግር ማውጣት አለበት ያሉት ደግሞ በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ አለማየሁ አበበ ናቸው።

በውጭም ይሁን በአገር ወስጥ ያሉ ዜጎች ኢትዮጵያን ከወራሪዎች ለመታደግ በጋራ የሚቆሙበት ወሳኝ ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

አንድነትን በማጠናከር መተባበር ከተቻለ የትኛውንም ጫና በመቋቋም አሸናፊ መሆን እንደሚቻልም አብራርተዋል።

በውጭ ምንዛሬ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንዲትሆን ዳያስፖራው ህጋዊ የገንዘብ መላኪያ መንገዶቸን መጠቀም፣ በልማትና ኢንቨስትመንት መሳተፍ እንዲሁም ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።

በተለይም ዳያስፖራዎች ለልማትና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ለተለያዩ እገዛዎች ወደ አገር ቤት ሲመጡ ያልተገባ ጥቅም የሚሹና ከአገራቸው ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ አንዳንድ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሹማምንቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰዋል።

ሆኖም በቀጣይ ሁላችንም ከራሳችን ቅድሚያ ለአገራችን በማሰብ ኢትዮጵያን ከችግርና ድህነት ለማውጣት በጋራ እንቁም ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም