የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና አሰባሳቢዎች ማህበር ተመሰረተ

119

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና አሰባሳቢዎች ማህበር ተመሰረተ።
በኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ የተመሰረተው ማህበሩ ከ200 በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በመያዝ ነው።

የኢትዮጵያ ደም ለጋሾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ብዙአየው ጌታቸው፤ የማህበሩ ምስረታ ዋና አላማ በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰተውን የደም እጥረት ችግር ለመፍታት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ማህበሩ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ልምዱ እንዲዳብር ለማስቻል የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት እንዲለግሱ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ በጎ ፍቃድኛ ወጣቶች የደም ለጋሾች ማህበር አባል እንዲሆኑ የማህበሩ አባላት እንደሚሰሩም  አቶ ብዙአየው ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በድሬዳዋና ሌሎች የክልል ከተሞች የማህበሩን እንቅስቃሴ በማስፋት የደም ልገሳ ባህል እንዲዳበር ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል በንቴ፤ በኢትዮጵያ የደም አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ብዙ መስራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የደም ልገሳ ማህበራት ምስረታ እውን መሆን ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በተለያዩ ክልሎች ያሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የደም ልገሳ በማድረግ እጥረቱን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው ይሄው በጎ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ21 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ክበባትን በማጠናከር የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበትና በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ማብዛት ይገባል ብለዋል።

ከማህበሩ መስራቾች መካከል ያነጋገርናቸው ወጣቶች ቀደም ሲል የደም ልገሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይም አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።

ደማችንን በመለገስ ውድ የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ማትረፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ ማህበሩ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ የደም ልገሳ በማከናወን እንዲሁም ደም ለጋሾች እንዲበራከቱ ቅስቀሳ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።