አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ ከጋዜጠኝነት መርህ ያፈነገጠ ነው

103

ጥቅምት 14/2014 ( (ኢዜአ)አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ ከጋዜጠኝነት መርህ ያፈነገጠ መሆኑን የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሁራን ገለጹ።
የአፍሪካን የሚወክል ጠንካራ ሚዲያ ሊቋቋም እንደሚገባም ነው ምሁራኑ ያነሱት፡፡

ገለልተኝነትና ትክክለኝነት ከጋዜጠኝነት አንኳር መርሆች መካከል ዋነኞቹ ቢሆኑም የተወሰኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ግን ከዚህ በተቃራኒው ሆን ብለው የተዛቡ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡   

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር ዶክተር ሙሉቀን አሰግደው እንዳሉት፤አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ለአሸባሪው ህወሃት የሚያደላ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው።   

ይህም መሰረታዊ ጋዜጠኝነት መርህን የሚጥስ እንደሆነ የገለጹት ምሁሩ "በስራዎቻቸው አንዱን አካል ተጠቂ ሌላውን ደግሞ አጥቂ አድርገው መሬት ላይ ያለውን እውነታ በካደ መልኩ እየዘገቡ ነው" ብለዋል፡፡   

ቴሌግራፍ የተሰኘው የዜና አውታር በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአርሲ አካባቢ የስንዴ ምርት በጎበኙበት ወቅት ያደረጉትን ንግግር አዛብቶ ያቀረበበትን ሁነት ለአብነት አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ "እንደዚህ ከተሰራ ወደ ፊት አንድም ስንዴ ወደ አገር ውስጥ አናስገባም" ያሉ ሲሆን፤ ቴሌግራፍ ይህን ሃቅ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ኪሎ ስንዴ እንዳይገባ ከለከሉ" ሲል መዘገቡን ነው የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ህወሃት በርካታ ሰለማዊ ዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ ቢሆንም የተወሰኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን አንድ ለአንድ ወገን ያደላ ዘገባን እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

ይህ በኢትዮጵያ ያለው ሃቅ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እንዳይሆን ከመሻት የመነጨ ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

ገለልተኛነት፣ፍትሃዊነት፣ሚዛናዊነትና ትክክለኝነት የጋዜጠኝነት አንኳር መርሆች መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተር ሙሉቀን፤ የውጭ ሚዲያዎች ይህን ካለማወቅ ሳይሆን ሆን ብለው ግጭት ለማባባስና ሊጠቅሙት ለሚፈልጉትን አካል የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ለመስጠት መረጃን አዛብተው እየዘገቡ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት የኮሚዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በማጠናከር የሀሰት ዘገባዎች ሲወጡ ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ የመመከት ስራ ማከናወን አለበት ብለዋል፡፡    

እንደ ዶክተር ሙሉቀን ገለጻ፤ በገለልተኝነት የሚሰሩ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ከመፍትሄዎቹ መካከል ጠቅሰዋል።  

ኢትዮጵያ ካላት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና ሚና አንጻር ትኩረት የሚደርግባት አገር መሆኗን ያስረዱት ምሁሩ፤ ይህንን ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

መገናኛ ብዙሃንን በሚመለከት ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገሮችን አስተባብራ የአፍሪካ ድምጽ የሚሆን መገናኛ ብዙሃን እንዲቋቋም የራሷን ሚና መወጣት አለባት ብለዋል።  

አልጀዚራ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከምዕራቡ የሚመጡ ትርክቶችን ለመመከት መቋቋሙን አስታውሰው፤ በአፍሪካም በተመሳሳይ ዓላማ የሚንቀሳቀስ ተወዳዳሪ መገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መወጣት አለባት ብለዋል።    

በጎንደር ዩኒቨርስቲ ጋዜጠንኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል የዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ምንይችል መሰረት በበኩላቸው "የተወሰኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በሚመለከት ግርምትን የሚያጭሩ የተዛቡ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው" ብለዋል።     

ለአብነትም ሴቶችና ህጻናት "በጸጥታ ሃይሎች ተደፈሩ፤ በሁመራ የጅምላ ግድያ ተካሄደ፤ በተከዜ ወንዝ ውስጥ ንጹሃን ተገለው ተገኙ" የሚሉ በምንጭ ያልተደገፉና ተዓማኒ ያልሆኑ ዘገባዎችን አንስተዋል።  

አሸባሪው የህወሃት ሃይል በገባበት አካባቢ ሁሉ ንጹሃንን እየገደለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ግን ይህን ተግባር ሆን ብለው ሽፋን እንዳልሰጡት ተናግረዋል።  

በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃ የወቅቱ ፈተና መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግሥት ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ በፍጥነት ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም