የናይጄሪያ የዲፕሎማቶችና ባለሀብቶች ልዑክ ጅማን እየጎበኙ ነው

191

ጥቅምት14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የናይጄሪያ አምባሳደርና የአፍሪካ ህጻናት ተሰጥኦ አግኝ ፋዉንዴሽን መስራችና ፕሬዚዳንት በዶክተር ኢንጂነር ኖዋህ ዳላጂ የተመራ የዲፕሎማቶችና ባለሀብቶች ልዑክ በጅማ ጉብኝት እያካሄዱ ነው።

የልዑክ ቡድኑ አባላት ትናንት ጅማ ሲደርሱ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂባ አባ ራያ እና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ እንዲሁም ሌሎች የከተማው የስራ ሃላፊዎች በአባጅፋር አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድረገውላቸዋል።አባላቱ በዛሬው እለት በከተማው የቱሪዝም መዳረሻዎችና የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እየጎበኙ ነው።

የልኡክ ቡድኑ ጉብኝት ዋና ዓላማም የጅማን ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ለማጎልበትና በጋራ ለመስራት መሆኑ ተገልጿል።የጅማ ታሪካዊ ቦታዎችንና የቱሪስት መስህቦች ላይ የበለጠ በመስራት ቱሪዝምን የኢኮኖሚው ምንጭ ማድረግ የጉብኝቱ አንድ አላማ መሆኑ ተመልክቷል።

ጎብኚዎቹ ከ150 አመት በላይ ያስቆጠረውን የጅማን ታሪካዊ ሙዝየም በመጎብኘት ባዩት ታሪካዊ ቅርሶች መደሰታቸውን ተናግረዋል።ዶክተር ኢንጂነር ኖዋህ ዳላጂ “የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የቆየን ግንኙነት ለማጠናከር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሰራለን” ብለዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በኢኮኖሚ ለማጠናከር አልመው ወደ ታሪካዊቷ ጅማ መምጣታቸውን ገልጸዋል።ከተማዋን ለሚጎበኙ ለዲፕሎማቶች በጅማና አካባቢው ያለው የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።