በቦረና በድርቁ የተጠቁ ወረዳዎች ተለይተው እህል በፍጥነት የማድረስ ስራ እየተከናወነ ነው

205

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቦረና በተለይ በድርቅ የተጠቁ ወረዳዎች ተለይተው እህል በፍጥነት ለማድረስ የማጓጓዝ እና የማከፋፈል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ ቀደም ብሎ ድርቅ እንደሚከሰት ባመላከተ ትንበያ መሰረት ከመደበኛ በጀት ውጭ 100 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል።

ከበጀቱ ውስጥ 20 ሚሊዮኑ ለውሃ አቅርቦት፣ 10 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለከብቶች መኖ ለማዋል መመደቡን በመግለፅ።

የዝናብ እጥረትን ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ የሚያደርሰውን አደጋ ለመቀነስም 27 ሺህ 330 ኩንታል እህል መፈቀዱን አንስተው፤ እስካሁን ባለው 17ሺህ 330 ኩንታል እህል ወደ አካባቢው ተጓጉዞ መድረሱን ገልፀዋል።

በድርቁ ተጠቅተዋል ተብለው ለተለዩ ሶስት ወረዳዎች እህል የማጓጓዝና የማከፋፈል ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዞኑ 26 ተጨማሪ ውሀ በቦቴዎች እንዲቀርብለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በመንግስትና በተለያዩ እርዳታዎች 18 ተጨማሪ ቦቴዎች ውሃ እያቀረቡ መሆኑንም ገልፀዋል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ የመንግስትና ህዝብ ጉልበት ተደምሮ የኢትዮጵያንና የክልሉን ችግር ለማቃለል ድጋፉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ድርቁን ምክንያት አድርገው ሃብት ለማጋበስ አካውንት ከፍተው በግለሰብና በቡድን የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ ሲሻ በመንግስት በኩል በተከፈቱ አካውንቶችና በአካል ቦታው ድረስ በመሄድ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ችግሩን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከሚከናወኑ ተግባራት በተጨማሪ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አማራጭ የውሃ አቅርቦት በአካባቢው ለማምጣት የአንድ ቢሊዮን ብር  ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ትልልቅ የመስኖ ስራዎችና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በዘላቂነት ከተያዙ መፍትሄዎች መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል።