አሸባሪው ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሶስት ወር ቀለብ እየተሰራጨ ነው

83

ጥቅምት13/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለችግር ለተጋለጡ ከ534ሺህ በላይ ወገኖች የሶስ ወር ቀለብ ዛሬ ማሰራጨት ተጀመረ።

 የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና  ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት  የቅድመ-ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ስርጭቱ የተጀመረው ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ነው።

ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት ፍጆታ የሚውል ቀለብ የሚሰራጨው በ14 ወረዳዎች ለሚገኙ ወገኖች መሆኑንም አስረድተዋል።

የሚሰራጨው ቀለብ 271ሺህ 600 ኩንታል  ስንዴ መሆኑን አስታውቀዋል።

ስርጭት ከሚደረግባቸው ወረዳዎች በርሃሌ፣ጭፍራ፣ አብአላ፣ ያሎ፣ እዋና አውራ ወረዳዎች እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ቡድኑ በፈንቲ-ረሱ፣ በቂልበቲ ረሱና አውሲ ረሱ ዞኖች ሥር በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች በፈጸመው ወረራ  የተፈናቀሉ 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በፌዴራልና በክልሉ መንግሥታት ድጋፍ ህይወታቸውን ሲመሩ መቆየታቸውን  አመልክተዋል።

ቡድኑ በንጹሃን አርብቶ አደሮች የግፍ ጅምላ ግድያና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም የቤት እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ዘረፋ ሲያደረግ መቆየቱን  አስታውሰዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ የፈጸመው ከሦስት ወራት በፊት ሲሆን፣በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣በክልሉ ልዩ ሃይልና ሌሎች የፀጥታ አካላት በደረሰበት ምት ክልሉን ለቅቆ ለመውጣት መገደዱ ይታወቃል።