የሕዝቡን ህልውና ለማስከበር አመራሩግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ ነው

112

ደሴ፤ ጥቅምት 13/2014 (ኢዜአ) የደሴና አካባቢው ሕዝብ ህልውናውን ለማስከበር በጀመረው እንቅስቃሴ አመራሩ ግንባር ቀደም በመሆን ሚናውን እየተጫወተ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ገለጹ።

ከንቲባው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ በየደረጃው የሚገኘው የከተማው አመራር በተለያዩ አደረጃጀቶች ተከፋፍሎ ህብረተሰቡን በማስተባበር የመሪነት ሚናውን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

አመራሩ  በቀዳሚነት የተሰለፈው  የአሸባሪው ህወሓት  ወረራ ለመቀልበስ    መሆኑንም አመልክተዋል።

አመራሩ ለነዋሪዎች የሚሰጠው አመራር  እየተገመገመ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፤ ከተቀመጠው አቅጣጫ ውጭ የሚንቀሳቀስ ካለ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የከተማው ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ከአመራሩና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ወራሪውን ቡድን በተባበረ ክንድ እንዲመክት አሳስበዋል።

”ወቅቱ ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን ጠብቀን፤ ተደጋግፈን፤ ተጋግዘና መስዋዕት ከፍለን ህልውናችን የምናስጥልበት ነው”ብለዋል።

ሕዝቡ አሸባሪውን የህወሃት ወራሪ ኃይል ”እሾህ ሆኖ መውጋት አለበት”ሲሉም ከንቲባው ተናግረዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ ላይ መሆናቸውን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች፤ንግድ ተቋማትና ባንኮች ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል፡፡