የትምህርት ፖሊሲው የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት በጥናት መለየቱ ተገለፀ

3359

አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት በጥናት መለየቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ136 በላይ ተመራማሪዎችን በማሳተፍ በፖሊሲው ትግበራ፣ ውጤትና ችግሮች ላይ ያተኮረ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል።

በጥናት ቡድኑ አማካኝነትም በዘርፉ አሉ የሚባሉትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁም ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል።

ይህንኑ በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዩ ጌቴ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው እንደጠቆሙት በኢትዮጵያ ላለፉት 24 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው የትምህርት ፖሊሲ ያስገኛቸው ጥቅሞች ቢኖሩም ፖሊሲውን በተገቢው መንገድ በመተግባር የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ረገድ  ችግሮች ነበሩበት።

የትምህርት ፖሊሲው የዜጎችን የትምህርት ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር ግብርናና ጤናን ጨምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰው ኃይል ቁጥሩ እንዲበራከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ሆኖም አሁንም የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

እነዚህን ጉድለቶች ለመሙላት መንግስት የተለያዩ ተግባራት ማከናወን መጀመሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችልና ከ136 በላይ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከትምህርት ፍትሐዊነትና ተደራሽነት በተጨማሪም ለጥራትና ተገቢነት ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል።

የትምህርት ጥራቱ በየደረጃው የሚመረቀውን ተማሪ በቂ እውቀት ያለው መሆን፤ አለመሆኑን ለመለየት ሚኒስቴሩ ባካሔደው የትምህርት ጥራት ማረጋጋጫ ጥናት ችግሮች እንዳለባቸው አረጋግጧል ነው ያሉት ዶክተር ጥላዬ።

 የትምህርት ፖሊሲው 24 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አገሪቱ የምታልመውን መካከለኛ ገቢ ያላቸው የዓለም አገራት ምድብ ለመቀዳጀት የሚያስችል አይደለም።

በመሆኑም ይህንን ህልም እውን ለማድረግ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ-ካርታም አገሪቱ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ የምትመራበት ይሆናል ብለዋል።

በመጪዎቹ ሳምንታት ከሚኒስትሮች፣ ከክልል ርእሰ-መስተዳድሮች፣ ከሲቪክ ማሕበራትና ከተለያዩ አካላት ጋር በፍኖተ-ካርታው ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በየደረጃው ግብአቶች ይሰበሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል።