በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር የተሰጠው የጎረቤት አገራት ወታደራዊ ትምህርታዊ ስልጠና ለቀጠናው ሰላም ጠቃሚ መሆኑ ተገለጸ

924

አዲስ አበባ ነሃሴ 12/2010 በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር የተሰጠው የጎረቤት አገራት ወታደራዊ ትምህርታዊ ስልጠና የደቡብ ሱዳንን መከላከያ ሰራዊት ለመለወጥ የሚያግዝ እንደሆነ ደቡብ ሱዳናውያን ወታደራዊ መኮንኖች ተናገሩ ።

የኢፌድሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እንዲሁም ወታደራዊ መኮንኖች በተገኙበት 130 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ዛሬ በዲፕሎማና በማስተርስ መርሃ ግብር ተመርቀዋል።

በዕለቱ አስር የወዳጅና የጎረቤት አገራት ከፍተኛ መኮንኖች ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁ ሲሆን የደቡብ ሱዳን፣ የቡሩንዲ፣ የሶማሊ ላንድና የፑንት ላንድ ወታደራዊ መኮንኖች ይገኙበታል።

ከምረቃው በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ የደቡብ ሱዳን ልዩ ኃይል ኮማንዶ ባልደረባ የሆኑት ኮለኔል ሰለሞን ቶር ካንግ ”የተሰጠኝ ዕድል እጅግ ብዙ ወታደራዊ ዕውቀቶችን እንድቀስም አድርጎኛል” ብለዋል።

በስልጠና ቆይታው ወቅት የደህንነት ስትራቴጂ ጥናት፣ የጦርነት ጥናት፣ ወታደራዊ አመራርና የሕብረት ውጊያ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን አግኝተው በማስተርስ መርሃ ግብር መመረቃቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱ የደቡብ ሱዳንና የቀጠናው ሰላም የተረጋገጠ እንዲሆን የጸጥታ ዘርፍ የሰው ኃይል ስልጠና በመስጠታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ኮለኔል ሰለሞን ወደ ደቡብ ሱዳን ሲመለሱ ያገኙትን ስልጠና ተጠቅመው የአገራቸውን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

”በአገሬ በሚስተዋለውና መፍትሄ ባጣው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መከላከያ ኃይሉ የተለወጠና ሕዝቡን የሚጠብቅ እንዲሆን እሰራለሁም” ብለዋል ኮለኔል ሰለሞን።

ሌላው ከዓመት በፊት እዚህ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ትምህርታዊ ስልጠና ወስዶ አገሩን ሲያገለግል የቆየው ብርጋዴር ጄኔራል ጆንግ አኮክ ዴግም የኮለኔል ሰለሞንን ሃሳብ ይጋራሉ።

አሁን በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ውስጥ የሚሊተሪ አታሼ ሆነው እያገለግሉ የሚገኙት ብርጋዴር ጄኔራል ጆንግ የኢትዮጵያ የድጋፍ መልክ ብዙ መሆኑን ይናገራሉ።

በወታደራዊ ስልጠና ዘርፍ ብቻ እሳቸውን ጨምሮ በሶስት ዓመታት 37 ደቡብ ሱዳናዊያን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና አዛዦች በኢትዮጵያ ስልጠና ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ስልጠና ካገኘው ደቡብ ሱዳናዊ ወታደራዊ መኮንንም አገራቸው ብዙ እንደምትጠብቅ ብርጋዴር ጄኔራል ጆንግ ያስረዳሉ።

በቀጣይም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጠናከርና የተጀመረው ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ ድጋፍም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን እያሰለጠነ የሚገኝ  ተቋም ነው።