ለተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል

86


ባህርዳር፤ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ጥቃት ምክንያት በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎች በ”ዩ ኤስ አይዲ ” በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ገለጹ።

አምባሳደሯ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታና በሰብአዊ ድጋፍ ላይ ያተኮረ ውይይት ከክልሉ የስራ ሃላፊዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ ነበር።


በጥቃቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ በጋራ መክረናል ብለዋል።


“ሁልጊዜም ግጭት ባለበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ድንበር የሌለው መፈናቀልና መሰደድ አለ” ያሉት አምባሳደሯ፤ የሚደርሰውን የህዝብ ስቃይና መከራ መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በማተኮር መወያየታቸውን አሰረድተዋል።


ባለፉት አስር ዓመታት በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ዶላር በ”ዩኤስ አይዲ ” በኩል ፈሰስ በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎችና በሌሎች የልማት ስራዎች በመደገፍ ኢትዮጵያን ማገዛቸውን አውስተዋል።


አሁን ላይ በአሸባሪው ህወሃት በተፈጸመው ጥቃት ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልጸው፤ ድጋፍ ከሚሹ ኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል።


ጥቃት ካለ የዜጎች መከራ፣ ስቃይና ሌሎች ችግሮች ይበዛሉ ያሉት አምባሳደር ጊታ፤ ዋናው የመንግስታቸው አቋም ጦርነቱ የሚቆምበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን አስረድተዋል።


በ”ዩ ኤስ አይ ዲ” የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት አስተዳደሪ ሳራህ ቻርለስ በበኩላቸው፤ በአማራ ክልል ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለዋል።


በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ ምግብ፣ መጠለያ እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳጋጠማቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።


የአሜሪካ መንግስትና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ድርጅት ዋና ዓላማም ለተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎች የሚደረገውን ሰብአዊ ድጋፍ ማሳደግ ላይ ለመምከር መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፋቸውም በአሸባሪው ህውሃት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች ጭምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።


ዛሬ ጧት ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ባካሄዱት ውይይትም ለሚያደርጉት ድጋፍ የክልሉ መንግስት ትብብር እንደማይለያቸው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።