ወላጆች ህጻናት ልጆቻቸውን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል በወቅቱ እንዲያስከትቡ ጥሪ ቀረበ

113

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) ወላጆች ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ልጆቻቸውን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል በወቅቱ እንዲያስከትቡ ጥሪ ቀረበ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ ከ65 ሺህ በላይ ህፃናትን የሚከተቡበትን ዘመቻ ዛሬ ያስጀመሩት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ ሀገር ተረካቢ ህፃናት  ጤናቸው ሊጠበቅ ይገባል፡፡

ወላጆች ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በወቅቱ በማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ፤  የፖሊዮ / የልጅት ልምሻ/ ክትባቱ በየጊዜው በመደበኛነት ቢሰጥም በሽታ የመከላከል አቅማቸው እንዲጎለብት የፖሊዮ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል  በዘመቻ መልክ ይሰጣል ብለዋል፡፡

በሽታው በድሬዳዋ በመልካ ጀብዱ ቀበሌ በሽታው ምልክት በመታየቱ ቤት ለቤት ክትባቱ መሰጠት አስፈልጓል ብለዋል፡፡

 የክትባት ዘመቻው የፖሊዮ በሽታ ስርጭትን ለመግታትና ለማጥፋት የህጻናትን በሽታውን የመከላከል አቅም ለማጎልበት የሚሰጥ ነው ያሉት ወይዘሮ ለምለም ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት ክትባቱ ለህጻናት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡  

የኮቪድ መከላከል መንገዶችን በመተግበር በድሬዳዋ በገጠር በከተማ ከ65 ሺህ  በላይ ህጻናት የሚከተቡ ሲሆን ክትባቱን በ219 ቡድኖች የተዋቀሩ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን መስጠት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ጤና ጣቢያ ህጻናት ልጆቻቸውን ሲያስከትቡ የነበሩት ወይዘሮ ፍቅርተ ሽመልስ ፤ ክትባቱ ልጆቻቸው ጤናማና ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስቸል መሆኑን በመረዳት በወቅቱ ማስከተባቸውን ተናግረዋል፡፡

ህጻናት ማስከተብ እፎይታ የሚሰጥ በመሆኑ ወላጆች በወቅቱ የማስከተብ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም