በኢትዮጵያ 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕፃናት የፖሊዮ ክትባት ይከተባሉ

74

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 12/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በዚህ ወር በሚካሄደው የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ)መከላከያ ክትባት 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕፃናት እንደሚከተቡ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው በሐዋሳ የክትባት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ዛሬ እንደተናገሩት ከጥቅምት 12 እስከ 15/2014 በመላው ሃገሪቱ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ይካሔዳል።

በኢትዮጵያ በመከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመተግበር በተለይ ፖሊዮን ለማጥፋት በተከናወኑ ተከታታይ ሥራዎች “ዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ” የተሰኘውን የልጅነት ልምሻ ዝርያ በ2009 ማጥፋት እንደተቻለ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ክትባት በጥራትና በሚፈለገው ሽፋን በማይሰጥባቸው ሥፍራዎች የሚቀሰቀስ የፖሊዮ ቫይረስ ዝርያ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች መከሰቱን ተናግረዋል።

ቫይረሱ በተቀሰቀሰባቸው ሥፍራዎች እስከ አሁን ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት በዘመቻ መልክ መከተባቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው ሀገር አቀፍ ዘመቻ በሁሉም ክልሎች እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕፃናት እንደሚከተቡ አስታውቀዋል።

በዘመቻው መደበኛውን የፖሊዮ ክትባት የወሰዱም ጭምር እንደሚከተቡና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ሕፃናት አንዲከተቡ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና ወላጆች እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ለዘመቻው አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንና ግብዓቶች መሟላታቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና 40 ሺህ ለሚጠጉ የጤና ኢክስቴንሽን ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ፖሊዮ ለበርካታ ዓመታት ሕፃናት ላይ ሕመምና አካላዊ ጉዳት ከማስከተሉም ባሻገር ለሞት እየዳረገ ያለ በሽታ ነው ብለዋል።

ሆኖም በሽታው የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት ለማስቀረትና ትውልድን ለማዳን መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከክትባቱ ዘመቻ ጎን ለጎን እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎችን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማቴ መንገሻ በክልሉ ከ837 ሺህ በላይ ሕፃናት በዘመቻው ተደራሽ እንደሚደረጉ ገልጸው "ክትባቱን ቤት ለቤት በመዘዋወር የሚሰጡ 1 ሺህ 786 ቡድኖች ተዋቅረዋል" ብለዋል።

መርሐ ግብሩ በተጀመረበት የሞቲቴ ፉራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ የእህታቸውን ልጅ ያስከተቡት ወይዘሮ ኮሚኒስት ዓለሙ "የፖሊዮ በሽታ በሕፃናት ላይ አስከፊ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ክትባት መሰጠቱ እጅግ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የሲዳማና ደቡብ ክልሎች አመራሮች እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላትና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም