በዞኖቹ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 123 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሥራዎች ተከናውነዋል

144

መቱ /ጊምቢ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) በኢሉአባቦርና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በክረምት የበጎ ፈቃድ የዜግነት አገልግሎት ከ123 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሰብአዊ ድጋፍና የልማት ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ከክረምት ባለፈ በበጋው ወቅት እንዲከናወን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በኢሉ አባቦር ዞን ከሰኔ 2013 መጨረሻ ጀምሮ በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ የዜግነት አገልግሎቶች የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የዞኑ ወረዳዎች ዕውቅና ተሰጥቷል።

የዞኑ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዛራ አሚድ እንደገለጹት በዞኑ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልገሎት የዜግነት መርሀ ግብር  ከ92 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሰብአዊ ድጋፍና የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

በአገልግሎቱ የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራት፣ እርሻ ማረስና ሰብላቸውን ማረም፣ የደም ልገሳ፣ የተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ማሟላት፣ የመማሪያ ክፍሎችን መስረትና ማደስን ጨምሮ በ30 የተለያዩ ዘርፎች ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሚ የሚያደርገው አቅም የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው።

መርሀ ግብሩ የዜጎችን አንድነትና እርስ በርስ የመረዳዳት ባህል ከማዳበር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

"በመሆኑም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ከክረምት ባለፈ ዓመቱን ሙሉ የሚከናወን ተግባር እንዲሆን ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ የዜግነት መርሃ ግብር ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ ግለሰቦችም ተግባሩ ለሕሊና እርካታን የሚሰጥና መተሳሰብን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዱጋባስ ዱጉማ አንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግለሰቦች ለብቻቸው ማድረግ የማይችሉትን በመተባበር ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው።

"በአገልግሎቱም ከትንሽ አስከ ትልቅ ችግር መፍታት የሚያስችል ሥራ ማከናወን ይቻላል" ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ ስራው ቤታቸው የተሠራላቸው ወይዘሮ ደጊቱ ኡመታ በበኩላቸው ለብዙ ዓመታት  የኖሩበት ደሳሳ የሣር ክዳን ቤታቸው ወደ ቆርቆሮ በመቀየሩ ለብርድና ዝናብ ከመጋለጥ መዳናቸውን ገልጸዋል።

"ሰው ለሰው መድኃኒቱ ስለመሆኑ ለእኔ በተደረገው ድጋፍ አይቻለሁ" በማለት ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል።

በኢሉባቦር ዞን በአጠቃላይ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ከ252 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በስራዎቹም ከ993 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

በመርሀ ግብሩ የተሻለ አፈጻጸም ላላቸው  ወረዳዎች እውቅና ተሰጥቷል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ23 ወረዳዎች ከ380ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ መሰራቱ ተገልጿል፡፡

የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በበጎ ድቃድ አገልግሎት መርሀ ግብሩ ወጣቶችን ጨምሮ 131 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ መስቀሌ ቶለሳ እንዳሉት በዞኑ በ23 ወረዳዎች ለሦስት ወራት በተሰጠው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በአገልግሎቱም  ለ193 አቅመ ደካሞች አዳዲስ ቤቶች ሲገነቡ የ99 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችም መታደሳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።  

በህብረተሰቡ ተሳትፎ 93 የእንጨት ድልድዮች መገንባታቸውንና 384 ዩኒት ደም መሰብሰቡን ጠቁመው

የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍና የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ስራዎችም በመርሀ ግበሩ መከናወናቸውን አመልክተዋል ።

እንደ ሀላፊዋ ገለጻ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 31ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሰብአዊ ድጋፍና የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

በመርሀ ግብሩ 382ሺህ 441 የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የገለጹት ሃላፊዋ፣ የህብረተሰቡ የመተሳሳብና የመረዳዳት ባህል እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግስትን የለውጥ ሥራዎች ከመደገፍ ባለፈ በመንግስት በጀት ያልተሸፈኑ የልማት ስራዎችን  በመስራት ማህበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

መርሀ ግብሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጣቱ በበጋ ወራትም አገልግሎቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሀላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም